ቀጥታ፡

ችግሮች በምክክር ብቻ እንደሚፈቱ በማመን እኔና ቡድኔ በምክክሩ እየተሳተፍን ነው - ተመካካሪ ጃል ሰኚ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፦ ችግሮች በምክክር ብቻ እንደሚፈቱ በማመን እኔና ቡድኔ በምክክሩ እየተሳተፍን ነው ሲሉ ተመካካሪ ጃል ሰኚ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ስምንት የምክክር አጀንዳዎችን በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ምክክር እያካሄደ ይገኛል።

ተመካካሪ ጃል ሰኚ ምክክሩን አስመልክተው እንዳሉት፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ በአጀንዳዎች ላይ ሰፊ ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት የቆዩ ልዩነቶችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር መዘጋጀቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን እየተካሄደ በሚገኘው ምክክር በመሳተፍ ያላቸውን ሀሳብ በማንጸባረቅ እየመከሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በምክክር ሂደቱ በ10 እና 50 ስብስብ በመሆን በአጀንዳዎች ላይ መወያየታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ 250 ሆነው በመምከር ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

በምክክሩም በአጀንዳዎች ላይ ሃሳባቸውን በነጻነት ሲያንሸራሽሩ እንደነበር ያነሱት ተመካካሪ ሰኚ ነጋሳ፤ ከሁሉም ተሣታፊዎች ጠንካራ ሃሳቦች መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

እርሳቸውና ቡድናቸው ከዚህ ቀደም የትጥቅ ትግልን በመምረጥ ጫካ ገብተው እንደነበር አስታውሰው፤ ችግሮችን በመሳሪያ ከመፍታት ይልቅ በሰላማዊ የምክክር መድረክ መፍታት ጥሩ አማራጭ መሆኑን በማመን ወደ ሰላም መንገድ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ችግሮቻቸውን በምክክር የፈቱ ሀገራት በሁሉም ዘርፍ ዕድገት በማሳየትና ተጽዕኖ በመፍጠር እድገት በማስመዝገብ ታላላቅ ሀገራት መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ችግሮችን በምክክር መፍታት ያልቻሉና ወደ ግጭት ያመሩ ሀገራት፤ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ተዳክመው ለከፋ ድህነት መዳረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን እየተካሄደ ያለው ምክክር ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታትና ለዘላቂ ሀገራዊ እድገት መሠረት የሚጣልበት ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሮች ባህል እንዲሆኑ መስራት ተገቢ መሆኑን አመልክተው፤ የምክክር ባህል ማደግ ለማንኛውም ችግር ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የተለያዩ አጀንዳዎቻቸውን በማቀራረብ የጋራ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻልም ጠቅሰዋል፡፡

በሀገሪቷ የሚገኙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዲሁም ሁሉም አካላት ተገናኝተው በመመካከር ሃሳብ መለዋወጣቸው አዎንታዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ሂደት በሀገሪቷ ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ ከፍተኛና አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም