ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በእውቀትና በሥነ-ምግባር የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት ይጠበቅባቸዋል

መቱ ፤ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ) :-ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገበያው የሚፈልገውን በእውቀትና በሥነ-ምግባር የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው ተመላከተ።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛውን ዙር የውጤት ተኮር የሥርዓተ-ትምህርት ክለሳና ማረጋገጫ ወርክሾፕ እያካሄደ ይገኛል።


 

በወቅቱም በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርትና ፕሮግራሞች ዴስክ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ነገዎ እንዳሉት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገበያው የሚፈልገውን በእውቀትና በሥነ-ምግባር የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በሥርዓተ-ትምህርት ቀረጻ ወቅትም በአካባቢያቸው ያለውን አቅም ወደ ውጤት መቀየር ላይ ማተኮር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

ለዚህም የሥርዓተ-ትምህርት ቀረጻን ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና ከገበያው ፍላጎት ጋር ማጣጣም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ተቋማቱ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የትምህርት ዓይነቶችን እና የሰው ኃይልን በጥራት ለማፍራት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮችና የምርምርና ማኅበረሰብ ትስስር ምክትል ፕሬዚዳንት  በድሉ ተካ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በጤናና በተፈጥሮ ሳይንስ መስኮች ላይ ያተኮሩ የ17 የትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳና ማሻሻያ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ፕሮግራሞቹም የትምህርት ጥራትን፣ ተገቢነትንና የገበያውን ሁኔታ መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን አክለዋል።

ለውጤታማነቱም ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ተቋማት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ወርክሾፕ ላይም በዩኒቨርሲቲው የተቀረጹ 17 ፕሮግራሞች እንዲገመገሙ በማድረግ ውጤት ተኮር ስርዓተ ትምህርትን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር  ድርባ ገመቹ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይም የትምህርት ሚኒስቴር፣ የዩኒቨርሲቲው ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም