በክልሉ የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል
ሆሳዕና ፤ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ) :- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።
በክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ክልላዊ የከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።
በወቅቱም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንደገለፁት፤ በክልሉ የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ለዚህም አመራሩ የጋራ ትርክትን በመገንባትና ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ በመሥራት ለአካባቢው ፈጣን ልማት መረጋገጥ መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል።
በዋናነትም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ መስኮች የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ለሕብረተሰቡ የመልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማረምና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ሥራ በማከናወን ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የክልሉ አመራር በፓርቲው መርህ ላይ ተመስርቶ ማኅበረሰቡን ማገልገል እንዳለበት ተናግረዋል።
የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ከመፍጠር ባለፈ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡን ያሳተፉ የንቅናቄ ተግባራትን በማከናወን እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን ማጠናከር እንደሚጠበቅም ኃላፊው አመልክተዋል።