ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ቀልጣፋ የመንግስት አሰራር እንዲሰፍን እያደረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ) :-መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ቀልጣፋ የመንግስት አሰራር እንዲሰፍን እያደረገ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

በፌዴራል ደረጃ በአዲስ አበባ የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋት ዘመናዊ አገልግሎት እየተፈጠረ ነው። 

በዚህም አገልግሎቱ በተጀመረ አንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ 102 ማዕከላት፣ ሦስት ተንቀሳቃሽና አንድ የተቀናጀ መተግበሪያ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ 

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ አማራጮችም 953 ተቋማትን በማስገባት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ 

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥትን አገልግሎት ጥራት በማሻሻል የተገልጋዮችን እርካታ በማሳደግ የመልካም አስተዳደር ሥርዓትን እያሰፈነም ይገኛል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን ፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በሀገር ደረጃ ትልቅ የለውጥ እርምጃ እንዲሁም የመልካም አስተዳደርና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና አመራር ትምህርት ክፍል መምህር ኡጁሉ ኡኮክ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ህዝቡ ለአንድ አገልግሎት ወደተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መመላለስ ሳይጠበቅበት ጊዜውንና ገንዘቡን በአግባቡ እንዲጠቀም የሚያስችል ትልቅ ማሻሻያ ነው።

አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ ከብልሹ አሠራር የጸዳ ሥርዓት በመፍጠር ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን ገልጸዋል። 

ይህ አሰራር ብልሹ አሰራርን በማስቀረት፣ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥንና መልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። 

በተመሳሳይ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የልማታዊ ተግባቦትና የሚዲያ ጥናት መምህርና ተመራማሪ  ዘለቀ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቱ ህብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ላነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን አንስተዋል። 

መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ከዚህ ቀደም የነበረን መጉላላት በማስቀረት የተቀላጠፈ፣ ምቹና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለማግኘት ማስቻሉ ለዜጎች ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ማደራጀት የተገልጋዩን ጊዜና ወጪ በመቀነስ የመንግስትን የአሰራር ቅልጥፍናና ከህዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ትልቅ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።

አሰራሩ በአፍሪካ ደረጃም በጥሩ አርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም