ቀጥታ፡

በክልሉ በግብርና ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ሀረር፤ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ) :- በሐረሪ ክልል በግብርና ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ኡመር ተናገሩ። 

በክልሉ የ2018 የግብርና ልማት እቅድ አፈጻጸምና የ2019 የግብርና ልማት መሪ እቅድ ላይ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ኡመር፤ በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በገጠር ወረዳዎች በመስኖ ልማት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ  በቤተሰብ ደረጃ ጭምር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በተለይም የእንስሳት ተዋጽኦ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ትልቅ እመርታ የተገኘበት ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባሻገር የምግብ ዋስትና መሰረት መሆኑን አንስተው በተያዘው በጀት ዓመትም በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

በግብርና ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቢሮው የእቅድና ክትትል ዳይሬክተር ሚልኬሳ አህመድ፤ በበጀት ዓመቱ ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል ውጤትም አስገኝተዋል ብለዋል።


 

በግብርና ዘርፍ በሰብል ልማት፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርታማነት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የግብርና ባለሙያው መሳይ ስለሺ፤ በክልሉ የአርሶ አደሩ ምርታማነትና ተጠቃሚነት ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን አንስተዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እመርታዊ ለውጥ እያስገኙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመድረኩ በ2018 በጀት ዓመት በግብርና ልማት ተግባራት አበረታች ስራ ላከናወኑ የወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት፣ የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎች አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም