ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኸር እርሻ እስካሁን ከ385 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

ደብረ ማርቆስ ፤ሃምሌ 22/2018(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኽር ወቅቱ እስከሁን ከ385 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ስብሎች ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢአለ አለኽኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በያዝነው የመኸር  ወቅት ከእለት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት በትኩረት እየተሰራ ነው።

በምርት ወቅቱ  ከ669 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 26 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

እስካሁን በተደረገ ጥረት ከ385 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል ።

በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ በሎቄ፣ ማሽላ፣ የቢራ ገብስ፣ ጤፍና ሌሎች ገበያ ተኮር ሰብሎች መዘራታቸውን ጠቅሰዋል።

በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን በመስመር እንዲሁም  ከ229 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው ደግሞ በኩታገጠም የተዘራ መሆኑን አብራርተዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገ ጥረትም ከ660 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
የመኸር እርሻው ከ390 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዞኑ የጎዛምን ወረዳ የሸበልማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አንሙት የሻንበል እንደገለጹት የክረምቱን ዝናብ በመጠቀም ከአንድ ሄክታር በላይ መሬታቸውን በበቆሎና በስንዴ ሰብል መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

ምርታማነታቸውን ለማሳደግም የግብርና ባለሙያን ምክረ ሃሳብ በመከተል ማዳበሪያ በመጠቀም፣ በኩታ ገጠምና በመስመር መዝራታቸውን አስረድተዋል።

የቀበሌው ነዋሪ አርሶአደር ይበልጣል ካሴ በበኩላቸው ባቄላ፣ ገብስና በቆሎ ሰብሎችን ቀድመው መዝራታቸውን ጠቁመው ጤፍ ለመዝራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም