ቀጥታ፡

በክልሉ 51 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ):-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 51 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የመስኖ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አየልኝ መሳፍንት ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን ግንባታ በማስፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ  ይገኛል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም አርሶ አደሩን ከባህላዊ አሰራር በማላቀቅ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት የሚችልበትን እድል ከማስፋት አንፃር የተሻለ ስራ ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።

ለመስኖ ልማት የሚውሉ አካባቢዎችን በጥናት ከመለየት ባለፈ ወደ ግንባታ በማስገባት አርሶ አደሩ  የዘመናዊ መስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።

በተቀናጀ መንገድ በተደረገ ጥረትም 90 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ወደ ግንባታ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ 51 የሚሆኑትን በማጠናቀቅ ለልማት ስራ እንዲውሉ ለማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ግንባታቸው የተጠናቀቁ የመስኖ ፕሮጀክቶችም ከ3 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ያስቻሉ ሲሆን ከ 7 ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሆኑም ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከ30 ሺህ ሄከታር በላይ መሬት ማልማት የሚችሉ 99 የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይንን በማጠናቀቅ ለግንባታ ስራ ዝግጁ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

የመስኖ አውታሮችን በማስፋት የአርሶ አደሩን ትርፍ አምራች በማድረግ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ አቅሙን የማሳደግ ስራ ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ ነው።

እንዲሁም እንደ ሀገር በምግብ እህል ራስን የመቻል ግብ እንዲሳካ በሚያግዝ አግባብ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ለመስኖ ተቋማት ግንባታና ተያያዥ ስራዎች ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመትም ቀደም ሲል ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ግንባታ በማስገባት ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ እየተገባ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በመስኖ መልማት የሚችል ከ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዳለም ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም