በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው
ሮቤ፣ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ)፦በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የመስክ ምልከታ እያካሄዱ ነው።
አመራሮቹ ''ውጤታማ ተግባቦት ለጠንካራ ፓርቲ''በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለት ቀናት በባሌ ሮቤ ሲያካሂዱት የነበረውን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ መድረክ ካጠናቀቁ በኋላ ነው የመስክ ምልከታውን የጀመሩት።
በብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በዞኑ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል በግብርናው መስክ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው።
በተለይ አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በኩታ ገጠም ልማት እያከናወነ የሚገኘውን ጥረት በማሳያነት አቅርበዋል።
እንዲሁም ዞኑ ዝናብና የሌሎች የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ማልማት የሚቻልበት መሆኑን በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አርሶ አደሮች ከሚያለሙት ልማት ተጠቃሚ በመሆን፣ ኮምባይነርና ትራክተር በመግዛት ወደ ግብርና ሜካናይዜሽን እየተሸጋገሩ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የገጠር ሽግግርን ለማፋጠን ያለው እገዛ ከፍተኛ መሆኑንም አክለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች የመስክ ምልከታ የዞኑን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳትና በማስተዋወቅ፣ ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ የቀሰሙትን ልምድ እንዲያሰፉ ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።
በዞኑ በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች የተሸፈነ ሲሆን፣ ከልማቱም ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ ናቸው።
በተለያዩ የሰብል ዘሮች እየለማ ከሚገኘው ልማት 80 በመቶ የሚሆነው በሜካናይዜሽን በመታገዝ በኩታ ገጠም አሰራር የለማ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ በመኸር፣ በበልግና በመስኖ አማራጮች ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚለማ ሲሆን፣ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዓመታዊ ምርት እንደሚመረትም አመልክተዋል።
ለዚህም በልዑካን ቡድኑ የተጎበኘው የበጋ ስንዴ ልማት አንዱ ማሳያ መሆኑን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ጉብኝቱ በዞኑ የሚገኙ አማራጮች ይበልጥ እንዲተዋወቁ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
የአመራር አባላቱ በሮቤ ከተማ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሀሳብ ዐሻራቸውን ያኖሩ ሲሆን፣ ጉብኝታቸውን በመቀጠልም የአካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እንደሚጎበኙም ታውቋል።