ቀጥታ፡

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዲጅታሉ ዓለም ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት አስችሏል

ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጎች ለማፍራት እያስቻለ መሆኑን  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለፀ።

የቢሮ ኃላፊው አቶ ሰላሙ አማዶ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በክልሉ በዲጅታል ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ተጨባጭ ዉጤት እየተመዘገበበት ነው።

በጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ234 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ስልጠናውን የተከታተሉ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ስልጠናውን ከወሰዱት ዜጎች መካከል 185 ሺህ 8 መቶ በላይ የሚሆኑት የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተው የኦን ላይን ስራዎች ላይ በመሳተፍ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዳገኙም ገልፀዋል።

ቢሮው በዲጅታል ቴክኖሎጂው በቂ እውቀት ፣ ክህሎትና እውቅና ያገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርት ፀጋነሽ ሞገስ በበኩላቸው ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዘርፉ የበረኝን እውቅት በማሻሻል በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳደሪ ለመሆን አስችሎኛል ነው ያሉት።

ስልጠናውን አጠናቀው ባገኙት የእዉቅና ሰርተፍኬት ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝላቸው ስራን ለመስራት እንደቻሉ ነው የተናገሩት።


 

በሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርት ተስፋ በቀለ በበኩሏ፤ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ እዉቀትንና ክህሎትን ማሳደጋቸው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ጨምሮልኛል ነው የሚሉት።

የአትዮ ኮደርስ ስልጠናም በዘርፉ የነበረኝን እውቀት እንዳሻሽልና  በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን ተጠቃሚነቴን ለማሳደግ አስችሎኛል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም