የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 9 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 9 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ) :-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 9 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
አየር መንገዱ በ2018 በጀት ዓመት ውጤማ የስራ እንቅስቃሴ ማድረጉንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ አየር መንገዱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 9 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል።
ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፤ በ2018 በጀት ዓመት ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር የ9 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
አራት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች መክፈቱን ጠቁመው፤ 20 ነጥብ 7 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዙን ተናግረዋል።
22 የነበሩ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች ወደ 25 ከፍ እንዲል መደረጉን ጠቁመው፤ ይህም የሀገር ውስጥ አገልግሎት አቅም ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።
897 ሺህ ቶን ጭነት የማጓጓዝ አገልግሎት መስጠቱን ገልጸው፥ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።
እንደ አቶ መስፍን ገለጻ አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ 9 አዳዲስ አውሮፕላኖች በግዥ እና በኪራይ ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።