በሸገር ከተማ ባለፈው በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ ባለፈው በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል
ሸገር፣ ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፡-በሸገር ከተማ በ2018 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ቢንያም ፀጋዬ በ2018 በጀት ዓመት በከተማው ያለውን የተፈጥሮ እና ሰው-ሰራሽ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በከተማው የቱሪዝም መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ወደ ከተማዋ የሚደረገውን የቱሪስቶች ፍሰት ለመጨመር የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በከተማዋ ጥንታዊና ታሪካዊ የሃይማኖት ተቋማትን፣ በገፈርሳ ሐይቅ የሚካሄዱ የእሬቻና መልካ አቴቴን የመሰሉ የኦሮሞ ህዝብ በዓላት የሚከበሩባቸውን ስፍራዎች በማልማት የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ እንስሳትና አእዋፋት የሚገኙበት የኤግዱ እላላ፣ ሌሎች ውብ ተራሮችና አስደናቂ የመሬት አቀማመጦችን ለቱሪስት ምቹ በማድረግ፣ የቱሪስቶችን ፍሰት ከማሳደግም ባለፈ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት 500 ሺህ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ በማቀድ በተደረገው እንቅስቃሴ ከ1 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ጎብኚዎች ከዕቅድ በላይ መፈፀም መቻሉን ተናግረዋል።
እንዲሁም ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከተማዋን መጎብኘታቸውን ኃላፊው ጠቁመው፣ በአጠቃላይ ከቱሪዝም ዘርፉ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
በከተማዋ በተከናወኑ ተግባራት ዘርፉ ገቢን ከማስገኘት ባለፈ ለዜጎች በርካታ የሥራ እድሎችን እየፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።
በ2019 በጀት ዓመትም በከተማዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስፋፋት፣ የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት ለመጨመርና የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አስረድተዋል።