ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኝ ነው - ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኝ ነው - ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ስምንት የምክክር አጀንዳዎችን በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው ምክክር አራት ሺህ ተመካካሪዎች እየመከሩ ይገኛሉ።
ተመካካሪዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የምክክር መድረኩ የሁሉም ሐሳቦች የተካተቱበት፣ ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተመካካሪዎች መካከል አቶ ዮሴፍ ሰንበታ እንደገለጹት፤ በምክክሩ የሚሳተፉ ዜጎች በአጀንዳዎች ላይ ሐሳቦችን በነፃነት እያንሸራሸሩ ይገኛሉ።
በምክክሩ እየተነሱ ያሉ ሐሳቦች ሀገርን ከማዳን አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተው፣ ከምክክር ሂደቱ በኋላ ኢትዮጵያ ወደተሻለ ደረጃ እንደምትሸጋገር ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
ምክክሩ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አልፎ ለዓለም ተምሳሌት የሚያደርጋት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የምክክር ሂደቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በአንድነት ያሳተፈ ታሪካዊ መድረክ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ብርቱካን ይታየው ናቸው።
በምክክሩ ሰፊና ለአገር ዕድገት የሚበጁ አሻጋሪ ሀሳቦች እየተንጸባረቁበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል።
ተመካካሪ አቶ ያየህይራድ በለጠ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የነበሩ አለመግባባቶችን ከመሠረቱ በመፍታት ሀገርን ወደ ላቀ ጥንካሬና ከፍታ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያውያን በምክክር ሀገራቸውን እንደሚያሻግሩ የሚያስመስክሩበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክሩ አማካኝነት የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅምን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል።