ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም እያደገ መጥቷል-ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የማሳደግና እና ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ መድረክ አካሂዷል።


 

በተጨማሪም ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ የመላክ የላቀ  አፈጻጸም ላሳዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።

ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የላቀ ሚና አበርክቷል።

በአምራች ዘርፉ የሚመሩ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ዘርፉን የማነቃቃትና የመደገፍ ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ካውንስል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ተቋቁሞ፣ የኢንዱስትሪዎችን ችግር ከመለየት ጀምሮ በዘላቂነት ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

በዚህም በዘርፉ የነበሩ ማነቆዎች ለይቶ መፍትሔ በመስጠት ምርት እና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ችግሮች እንዲፈታ ታስቦ ተግባራዊ መሆን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በዘርፉ ከፍተኛ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል።


 

ይህ ንቅናቄ ሥራ አቁመው የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረጉን እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም እንዲሰማሩ ማስቻሉን ተናግረዋል። 

በዚህም ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጭ ንግድን በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና ማበርከቱን ጠቁመዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የፋይናንስ ማነቆ ለመፍታት በተወሰደ እርምጃ፣ ቀደም ሲል 40 ቢሊዮን ብር የነበረውን የብድር መጠን ወደ 115 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረግ ተችሏል።

"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በተጀመረበት ወቅት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ይቀርብ የነበረው የውጭ ምንዛሬ መጠን  አሁን ላይ  ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የኢንዱስትሪዎቻችን ተወዳዳሪነት፣ ምርታማነት፣ ትርፋማነት እና የመስፋፋት ዕድል ከፍ እያለ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከ2014 በፊት ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ ከ348 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያድኑ አልነበሩም ያሉት ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይ ግን 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረዋል። 


 

ይህም የንግድ ሚዛንን በማጣጣሙ በኩል የኢትዮጵያን ዘላቂ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን አብራርተዋል።

በወጭ ንግድ በኩል ቀደም ሲል ይገኝ የነበረው 385 ሚሊዮን ዶላር በዚህ ዓመት ወደ 607 ሚሊዮን ዶላር ማደጉን ጠቁመው፤ የአምራች ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራም ትልቅ አማራጭ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በ2019 በጀት ዓመት ከወጭ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

በእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት አምራቾች በበኩላቸው፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና አዳዲስ አቅጣጫዎች ለዘርፉ አዎንታዊ ሚና ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ሀብታሙ ዳርጌ፤ የተደረጉት የፖሊሲ ማሻሻያዎች የሪፎርም ስራዎች ለአምራቾች ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡


 

ማሻሻያዎቹ የምርት መጠናቸውንና ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳደገላቸው የገለጹት ደግሞ ህይወት ዳመኑ  ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም