አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአዘርባጃን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአዘርባጃን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፦የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአዘርባጃንን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሳሂባጋፋሮቫ (ዶ/ር) እና ከልኡካቸው ጋር ተወያይተዋል።
በዚህም በፓርላማ ትብብር፣ በኢኮኖሚ ግንኙነት፣ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት፥ ጉብኝቱ እየተጠናከረ የመጣውን የኢትዮጵያ እና አዘርበጃን ግንኙነት ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያንጸባርቅ አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በባኩ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በኢትዮጵያና በአዘርባጃን ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን አስታውሰዋል።
በተለይም አዘርባጃን ለኢትዮጵያ የ"መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማሻሻያ ያደረገችውን ድጋፍ በማድነቅ ትብብሩ በመንግሥት አገልግሎት ዘመናዊነት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች የምትገኘውን ሀገራዊ ሪፎርም በስፋት በማብራራት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሰላምና የብሔራዊ መግባባት ግንባታ ሂደትን ለማጠናከር ያለውን ሚና አብራርተዋል።
በተጨማሪም የአረንጓዴ ዐሻራና የኮሪዶር ልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ጥበቃን፣ ዘላቂ ልማትንና የከተሞችን ዘመናዊነት ለማፋጠን የሚያገለግሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በፓርላማ ዲፕሎማሲ ዘርፍ፣ የሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ቡድኖች በሕግ አወጣጥ፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በዲጂታል ፓርላማ ሥርዓት፣ እንዲሁም የሕዝብ ተሳትፎን በማጎልበት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ እንደሚችሉ ገልጸው በተለይ የወጣቶችና የሴቶች የፓርላማ አባላት ትስስር መጠናከር የሁለቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንደሚያሳድግ አንስተዋል፡፡