ሀገራዊ ምክክሩ ለህዝብ ጥያቄዎች እውነተኛ መፍትሔ ለማምጣት መሰረት የሚጥል ነው - ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለህዝብ ጥያቄዎች እውነተኛ መፍትሔ ለማምጣት መሰረት የሚጥል ነው - ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለህዝብ ጥያቄዎች እውነተኛ መፍትሔ በማምጣት ሀገራዊ አብሮነትን ለማጠናከር መሰረት የሚጥል መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማወያየት ምክክር የሚደረግባቸው ስምንት አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህም አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር እያደረጉ ነው።
በምክክሩ ላይ እየተየሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ምክክር እየተደረገ ይገኛል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ፓስተር አባይነህ ቦፌ እንደገለጹት ምክክሩ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ያካተተ ነው።
በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ምክክር ለኢትዮጵያ ሰላም ግንባታ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸው፤ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ምክክር እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፤ ይህ አካታች ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ መፍትሔ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ለዚህም በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ሀሳባቸውን በነጻነት እያንሸራሸሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ይህም ለህዝብ ጥያቄዎች እውነተኛ መፍትሔ ለማምጣት መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።