ቀጥታ፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን በመኸር ወቅት እርሻ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

አዳማ፤ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ሸዋ ዞን በመኸር ወቅት እርሻው ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት መታቀዱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በ2018/19 የምርት ዘመን ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው።


 

በዞኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት ለማልማት ታቅዶ ከነበረው ከ530 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ እስካሁን ከ475 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በተለያየ ምርጥ ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር መዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን ጠቅሰው፣ እስካሁን ከ800 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን ገልጸዋል።

የታቀደውን ምርት ለማግኘትም የግብርና ቴክኖሎጂ፣ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በስፋት ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰው፤ለአርሶ አደሩም ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የግብርና ምርቶችን የኤክስፖርት አቅም ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ በዕቅድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የኤክስፖርት ምርቶችን ለመጨመር በስንዴ፣በቦሎቄና በሽንብራ ላይ በሜካናይዜሽን የተደገፈ የኩታ ገጠም የሰብል ልማት እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

የዞኑን ግብርና ከበሬ ማረስ በማውጣት ወደ ሜካናይዜሽን ለማሸጋገር በተያዘው ዓመት 155 የእርሻ ትራክተሮች ተገዝተው በልማት ስራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በዞኑ ስንዴ፣ ቦሎቄ፣ ሽንብራ፣ ጤፍና ሌሎች ዋና ዋና ሰብሎች በ460 ክላስተር በመደራጀት እየለሙ መሆናቸውን ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም