አረንጓዴ ዐሻራ - የመደመር እሳቤ አንዱ ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ - የመደመር እሳቤ አንዱ ማሳያ
በየዓመቱ እያደገ የመጣው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በተጨባጭ ውጤት እየታጀበ የቀጠለ ሆኗል። ዐቅምን በመሰብሰብ በመደመር ዕሳቤ እየተከናወነ ያለው ይህ ኢኒሼቲቭ በረከቱ ብዙ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነትና አመራር ሰጪነት በ2011ዓ.ም የተጀመረው ይህ መርሃ-ግብር ዛሬ ላይ የዓለምን ትኩረት የሳበ ትልቅ ውጤትም እየተመዘገበበት ነው።
እንደየአካባቢው ሥነ-ምኅዳር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን ችግኞች፣ ለደን ሽፋን፣ ለከተማ ውበትና ለማረፊያ ጥላ የሚሆኑ የአፈር መከላትን የሚያስቀሩ ችግኞችን መትከል ባህል እየሆነም ነው።
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 184 ላይ እንደተጠቀሰው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ዋና ግብ የገጠርና የከተማ አረንጓዴ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ለሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና አስተዋጽዖ ማድረግ ነው።
ይህ መርሃ-ግብር በ2011 ዓ.ም ከመጀመሩ በፊት በ 2010 ዓ.ም. የነበረው ሀገር አቀፍ የደን ሽፋን 17 ነጥብ 2 በመቶ ነበር ።
በአንድ ሰው 40 ችግኝ (40 ዛፎች በነፍስወከፍ) በሚል መሪ ቃል በአንድ ቀን የተከናወነውን የአንድ ጀምበር የ 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኝ ተከላን ጨምሮ በተከናወነ መርሃ-ግብር የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ የሀገራችንን የደን ሽፋን በ2016 ዓ.ም 23 ነጥብ 6 በመቶ አድርሶታል።
የተለያዩ ክፍላተ-ዓለማት አንድም በከፋ ቅዝቃዜ እንዲሁም መደበኛ የኑሮ ሁኔታን በሚያናጋ አደገኛ ሙቀት ብሎም በድንገተኛ ጎርፍ እና ሰደድ እሳት በሚታመሱበት ጊዜ፤ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ቀድሞ ለማረቅ አንዱ መፍትሔ አረንጓዴ ዐሻራን በስፋት ማከናወን መሆኑ ይታመናል።
ባለፉት ዓመታት በብርቱዎቹ ኢትዮጵያውያን ርብርብ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፤ ውጤቱንም ሕዝቡ ዐይቷል።
በሕዝቡ ዘንድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ተፈጥሮን የመንከባከብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ጭምር ተደርጎ በመወሰዱ የተሳታፊዎች ቁጥርና የሚተከለው ችግኝ በየዓመቱ እየጨመረ ሊሄድ ችሏል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ጥቅሙ የሚታይ የሚጨበጥ ሆኗል። የመሬት ምርታማነትንም አሳድጓል። ከአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በፊት (በ2010 ዓ.ም) በሔክታር የሚመረተው ስንዴ 22 ኩንታል፣ በቆሎ 30 ኩንታል፣ ጤፍ 17 ኩንታል እንዲሁም ገብስ 23 ኩንታል ነበር።
ከኢንሼቲቩ ትግበራ በኋላ ደግሞ (በ2017 ዓ.ም) ስንዴ በሔክታር 36 ኩንታል፣ በቆሎ 46 ኩንታል፣ ጤፍ 20 ኩንታል፣ ገብስ 30 ኩንታል ማምረት ተችሏል። በዚህም መሠረት በ2017 ዓ.ም 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታር መሬት በስንዴ ሰብል በመሸፈን 280 ሚሊየን ኩንታል ማምረት ተችሏል።
ስንዴን በትጋት በማምረትም ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረን 1 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ተችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በፍራፍሬ ልማት ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል። በዚህም ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ ሕብረተሰቡ (አምራቹ) ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ በዚያው ልክ እንዲያድግ አስችሏል።
ይህም ኢትዮጵያም በአፍሪካ አቮካዶን በቀዳሚነት ወደ ውጭ የምትልክ ሁለተኛዋ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጠቀሜታ ዘርፈ-ብዙ ነው። የተፈጥሮ ስነ-ምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ በሁሉም መንገድ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ነው።
ከአረንጓዴ ዐሻራ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የባለድርሻ አካላት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር፣ በክረምት ወራት የሚተከሉ ችግኞችን በበጋ ወራት በአግባቡ መንከባከብ ከቀጣይ አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ በሆኑበት በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ወቅት አረንጓዴ ለሆነች ነገ፣ ሁላችንም ተስፋን እንትከል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለያዩ ዘርፎች የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በቀጥታ ለሕዝቡ ጥቅም የቆመ ሰው ተኮር መርሃ-ግብር መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።
ስለዚህ በቀጣይ ሕብረተሰቡ በመደመር ዕሳቤ በዚህ ኢኒሼቲቭ ላይ ያለጠባቂነት በንቃት የመሳተፍ ባሕሉን በማሳደግ ተጠቃሚነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መትጋት ይጠበቅበታል።