ቀጥታ፡

የበጋ መስኖ ስንዴ፤ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ የግብርና ዘርፍ እመርታ!!

በሚኪያስ ጎቡ

ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ አምድ፣ ሕዝብ የኑሮ መሠረትና የምግብ ዋስትና ማዕዘን ነው። በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ግብርና ዋነኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ሆኖ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ግብርናን ከኢንዱስትሪ፣ ከማዕድን፣ ከቱሪዝም እና ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር በመጣመር ወሳኝ የዕድገት ምሰሶ የሚሆንበትን ዕድል ፈጥሯል። ይህም በሰብል፣ በእንስሳት እና በሌሎች ዘርፎች እመርታዊ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል።

በዚህ ዘርፍ ከተመዘገቡ አስደናቂ ለውጦች መካከል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዲስ የዕድገት ፍኖት ከፍቷል። ለዓመታት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚያስፈልገውን ስንዴ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስታስገባ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ በስትራቴጂካዊ የግብርና ማሻሻያዎች፣ በመስኖ ልማት ማስፋፋት፣ በሜካናይዜሽን እና በአርሶና አርብቶ አደሮች አደረጃጀት የስንዴ ምርቷን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችላለች።

ይህ ለውጥ የገቢ ምርትን ከመተካት ባሻገር በምግብ ራስን መቻል፣ ለውጭ ንግድ አቅም እና ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት አዲስ ዕድል ፈጥሯል። የስንዴ ምርታማነትም በአርሶና አርብቶ አደሩ ዘንድ የይቻላል መንፈስን በማጎልበት የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ አቅም ፈጥሯል። ከዚህም በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና ሥርዓት በመገንባት ለአፍሪካና ለቀጣናው ሀገራት የልማት ተሞክሮ አስገኝቷል።

የምርትና የምርታማነት አብዮት

በክረምት ዝናብ ላይ ብቻ ተንተርሶ የቆየው የኢትዮጵያ ግብርና አሁን ዘመናዊ የአመራረት ምኅዋር ውስጥ ገብቷል። ይህም በቆላማ፣ በደጋማ እና በወንዝ ዳርቻ የሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወደ ምርታማ የስንዴ ማሳዎች ቀይሯል።

የስንዴ ምርታማነት አብዮትም በመስኖ፣ በሜካናይዜሽን፣ በተሻሻሉ የአመራረት ዘዴዎች እና በአርሶና አርብቶ አደሮች የተቀናጀ ጥረት የምርታማነትን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ አሻሽሏል። በዚህም ኢትዮጵያ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።

ይህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የግብርናን ገጽታ የቀየረ የምርትና የምርታማነት አብዮት ነው። ፖሊሲ፣ ቴክኖሎጂ፣ መስኖ እና የአርሶና አርብቶ አደሩ ትጋት ሲጣመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያጎናጽፍ አቅም መፍጠር እንደሚቻል የሚያሳይ የልማት ተሞክሮ ሆኗል።

የክላስተር ግብርና፤ የሜካናይዜሽን ስኬት እመርታ!!

የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ስኬት ከውጤታማ የአሠራር ዘዴዎች መካከል የክላስተር ግብርናና የሜካናይዜሽን አጠቃቀም ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው። ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና የሰብል ጥበቃ ግብዓቶችን በወቅቱና በተደራጀ መንገድ እንዲያገኙ አስችሏል።

የሜካናይዜሽን መስፋፋት ባህላዊ በሰው ጉልበትና በእንስሳት ኃይል የተመሠረተውን አሠራር በዘመናዊ ማሽነሪዎች በመተካት የማሳ ዝግጅትን፣ የዘር አዘራርን እና የምርት አሰባሰብን ውጤታማ አድርጓል። ትራክተርና ኮምባይነር አጠቃቀም የጊዜና የጉልበት ብክነትን ከመቀነሱ ባሻገር በምርት ስብሰባ ወቅት የሚደርሰውን ብክነት በመቀነስ የምርት ጥራትና መጠን እንዲጨምር አስችሏል።

የክላስተር ግብርናና የሜካናይዜሽን ሥርዓት የኢትዮጵያን የስንዴ ልማት ከተለመደው የኑሮ ግብርና ወደ ተወዳዳሪ የንግድና የኢንዱስትሪ ግብዓት ምንጭነት እንዲሸጋገር በማድረግ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።

የማክሮ ኢኮኖሚ አወንታዊ ተፅዕኖ፡- የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ለውጥ አምጥቷል። በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት መስፋፋቱ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በመተካት የምግብ ራስን የመቻል ግብን እያሳለጠ ይገኛል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከስንዴ አስመጪነት ወደ ላኪነት መሸጋገሯ የንግድ ሚዛንን በማሻሻል ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንዲፈጠር ዕድል ከፍቷል።

በሌላ በኩል የስንዴ ምርት መጨመሩ የምግብ አቅርቦትን በማረጋጋትና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በማጎልበት የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርታማነት የበለጠ ለማጠናከር እያስቻለ ነው።

የይቻላል ተምሳሌቱ፤ የበጋ ስንዴ ምርታማነት፡- የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት የግብርና ስኬት ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ አብዮትም ነው። ለዘመናት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማይቀር የሚመስለውን እሳቤ በመስበር ከጥገኝነት የመላቀቅ መንፈስን አጎልብቷል። በመስኖ የተደገፈ ዓመቱን ሙሉ የማምረት ባህልን በማስፋፋትም ለሌሎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ተነሳሽነት ፈጥሯል።

ከአፍሪካ ቀዳሚነት ወደ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ፡- የስንዴ ልማቱ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ አቅም በመፍጠር በአፍሪካ ቀዳሚ አምራች ሀገር አድርጓታል። የመስኖ ልማት መስፋፋትና ቆላማ አካባቢዎችን ወደ ምርታማ የስንዴ ማሳዎች መቀየር ለኢኮኖሚው ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ለአፍሪካ የተግባር ምሳሌ፡- የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለምሥራቅ አፍሪካና ለመላው አህጉሪቱ በምግብ ራስን መቻል እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል። የውጭ የስንዴ ገቢ ምርት ጥገኝነትን በማስቀረት በአፍሪካ ምድር የምግብ ሉዓላዊነት ሊረጋገጥ እንደሚችል ተጨባጭ ውጤት አሳይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች እንደገለጹት፤ ከስንዴ እርዳታና ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን በሀገር ውስጥ ምርት ማረጋገጥ እና መሬትና የመስኖ ውኃን በአግባቡ በመጠቀም ኢትዮጵያን ከምርት ተቀባይነት ወደ አምራችነትና ወደ ላኪነት ማሸጋገር እየተቻለ ነው።

ማጠቃለያ

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በኢትዮጵያ የተመዘገበ የግብርና ስኬት ብቻ አይደለም፤ የአስተሳሰብ፣ የፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ እና የሀገራዊ ቁርጠኝነት ፍሬ የሆነ የልማት አብዮት ነው። ለዘመናት የውጭ ጥገኝነት ምልክት ሆኖ የቆየውን የስንዴ አቅርቦት ችግር በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ኢትዮጵያ ከአስመጪነት ወደ ላኪነት የምትሸጋገርበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍታለች።

ይህ ስኬት የአንድ የግብርና ፕሮጀክት ውጤት ብቻ ሳይሆን መሬትን፣ ውኃን፣ ሳይንስን፣ ቴክኖሎጂን እና የአርሶ አደሩን ትጋት በአንድ ራዕይ ያስተሳሰረ የብልፅግና ሞዴል መሆኑን አሳይቷል። በተለይም የክላስተር ግብርና፣ የመስኖ ልማት፣ የሜካናይዜሽን መስፋፋት እና የተሻሻሉ የምርት ቴክኖሎጂዎች ተቀናጅተው ሲተገበሩ ግብርና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገር ኢኮኖሚን የመቀየር አቅም እንዳለው በተግባር አረጋግጧል።

ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው ይህንን ስኬት በማስቀጠል የጥራት ማሻሻያን፣ የእሴት ጭማሪ ኢንዱስትሪዎችን፣ የውጭ ገበያ ተወዳዳሪነትን እና የግብርና ዲጂታላይዜሽንን በማጠናከር ስንዴን ከምግብ ዋስትና ባሻገር የውጭ ምንዛሬ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት እና የሀገራዊ ኢኮኖሚ መረጋጋት ስትራቴጂያዊ ምሰሶ ማድረግ ነው።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የኢትዮጵያን ይቻላል መንፈስ በማሳየት የምግብ ራስን መቻልን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን፣ የውጭ ምንዛሬ አቅምን፣ የአፍሪካ የልማት ተምሳሌትነትን እና የቀጣይ ትውልድ የብልፅግና መሠረትን እየገነባ ነው። በዚህም የተገኘው የግብርና ድል የአንድ ወቅት የምርት ጭማሪ ሳይሆን የኢትዮጵያን የዕድገት ታሪክ የሚቀይርና ለአፍሪካም አዲስ የልማት አድማስ የሚከፍት ዘላቂ ስኬት ሆኖ ይቀጥላል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም