ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ93 ቢሊዮን ብር  በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የባህር ዳር ከተማ ገቢዎች መምሪያ "ግብሬን ደስ ብሎኝ እከፍላለሁ" በሚል መሪ ቃል የ2018 አፈፃፀም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ  አካሂዷል። 


 

የቢሮ ኃላፊው መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ስኬታማ ስራዎችን አከናውኗል ።

ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ100 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ ሲሰራ የቆየ ሲሆን የእቅዱን 92 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ለክልሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት በማዋል በራስ የመልማት አቅም ለመገንባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ነው የተናገሩት።

ቢሮው ከባህዳር ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮ-ቴሌኮም ኩባንያ ጋር በመተባበር በዲጂታል ግብር የመክፈል ስርአት መዘርጋቱ ለዘርፉ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ማበረከቱን አስረድተዋል።

ይህም ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው ግብር በመክፈል ፈጣን፣ ተአማኒነት ያለውና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም እሸቴ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 91 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

በተሰበሰበው ገቢም በከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎችን በማከናወን የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚውል እንደሆነም አስረድተዋል።

በ2019 በጀት ዓመትም የግብር አሰባሰብ ስርአቱን ይበልጥ ግልጽ፣ ፍትሐዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ለማድረግ በተሻለ መንገድ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ማጠናቀቂያ ላይም ለምስጉን ግብር ከፋዮችና ከፍተኛ ገቢ ለሰበሰቡ ተቋማት እውቅና የመስጠት ስነ ስርአት ተካሂዷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም