ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ልማት የተሰጠው ትኩረት በዘርፉ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል

ዲላ፣ ሐምሌ 21/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ልማት የተሰጠው ልዩ ትኩረት በዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠሩም በላይ  ቆይታችን እንድናራዝም አድርጎናል ሲሉ ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የመጡ ጎብኚዎች ገለጹ።

ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የመጡት ቱሪስቶች በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው ወቅት በኢትዮጵያ ባዩት የመዳረሻ ልማት፣ በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጥራት እና በህዝቡ እንግዳ አቀባበል መደሰታቸውን ቱሪስቶቹ ገልጸዋል።


 

ከስፔን የመጡት ዶክተር አና ፕካሶ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው አዲስ አበባን፣ ባህር ዳርን እንዲሁም የጌዴኦ ዞንን በጎበኙበት ወቅት ለቱሪስቶች እጅግ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተመልክተዋል። 

በጎበኟቸው የመዳረሻ ስፍራዎች ኢትዮጵያ የብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች እና የባህላዊ እሴቶች ባለቤት መሆኗን ለመረዳት መቻላቸውንም ጠቅሰዋል።

በተለይ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጥራት፣ በመዳረሻ ልማት እንዲሁም በህዝቡ እንግዳ አቀባበል መደሰታቸውን አንስተው፣ በዚህም የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም መወሰናቸውን ተናግረዋል።


 

በጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ውስጥ በተመለከቱት አስደናቂ የአካባቢ ጥበቃ ባህል መደነቃቸውን የገለጹት ደግሞ ከጣሊያን የመጡት ጎብኚ ኢንጅነር ሆሴ አንቶኒዮ ናቸው። 

ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች እንደ ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑን አመልክተው፣ በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት የተከናወኑ ተግባራት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ አናቤል ሮዲጌዝ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያዩዋቸው የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ቱሪስቶችን ለመሳብ ከፍተኛ አቅም ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።


 

 የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድርን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ባዩት ነገር መደሰታቸውን ጠቁመው፣ እንዲህ ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን የበለጠ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ልማት የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ቆይታቸውን እንዲያራዘሙ ማድረጉን ያነሱት ደግሞ ከስፔን የመጡት ካሮሊና ኢዩስካስ ናቸው። 


 

በቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ባዩት ነገር መደነቃቸውን በመግለጽ፣ እንዲህ ዓይነት አካባቢዎችን ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም ግብይትና ፕሮሞሽን ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በደቻ በበኩላቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዞኑ ያሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። 


 

በተለይም የይርጋጨፌ ቡና ባህላዊ ዝግጅትና ልዩ ጣዕሙ በርካቶች ዞኑን መዳረሻ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመትም ከ2 ሺህ የሚልቁ የውጭ እና ከ40 ሺህ በላይ የሚደርሱ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመቀበል ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ለዚህም በአሁኑ ወቅት ነባር እና አዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመለየትና በማልማት፣ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም