ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብ ሉዓላዊነትና ለዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብ ሉዓላዊነትና ለዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳአ ወረዳ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።




በመርሃ ግብሩ የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የኢንስቲትዩቱ አመራርና ሰራተኞች ተሳትፈውበታል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች እንዳሉት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት እየተተከሉ ያሉ ችግኞች ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በመርሃ ግብሩ የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች የአካባቢን ሥነ-ምሕዳር ከመጠበቅ ባሻገር፣ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የኢንስቲትዩቱ ባለሙያ የሆኑት በሻነ ጣሰው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ አሻራውን ሲያሳርፍ መቆየቱን ተናግረዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የመንከባከብና አርሶ አደሩን የመደገፍ ሥራ በኢንስቲትዩቱ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

እየተተከሉ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች የአካባቢውን ሥነ-ምሕዳር ከመጠበቅ ባሻገር፣ የአርሶ አደሩን የምግብ ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ቢቂላ ለሜሳ በበኩላቸው፤ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የተተከለው የአቮካዶ ምርት፣ ኅብረተሰቡ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ እያደረገው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው፤ እስካሁን ድረስ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ 500 ሄክታር መሬት በአቮካዶ የተሸፈነ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ክረምት ይህንን ወደ 700 ሄክታር ለማድረስ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ባጠቃላይ በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ተከትሎ የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳደጉት አመልክተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለመጪው ትውልድ ሥነ-ምሕዳሩ የተጠበቀና ምቹ አካባቢን የማሸጋገር ተግባር መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ሲኒየር ዳይሬክተር ደሳለኝ ድጉማ ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል በአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ላይ ትኩረት በመስጠት በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም የአቮካዶ ምርትን በክላስተር በማዘጋጀት ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም