ፍርድ ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ በሚሆኑ መዝገቦች ላይ ውሳኔ አሳልፏል - ኢዜአ አማርኛ
ፍርድ ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ በሚሆኑ መዝገቦች ላይ ውሳኔ አሳልፏል
ቦንጋ ፤ ሀምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ በሚሆኑ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር መዝገቦች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን ገለጸ ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት በዛሬው ውሎው የክልሉን መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድና ረቂቅ በጀት፣ እንዲሁም የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት የአፈጻጸም ሪፖርቶችና ጠቋሚ ዕቅዶች አድምጧል።
በወቅቱም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማርያም፤ ፍርድ ቤቱ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ በሚሆኑ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር መዝገቦች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።
የዳኝነት ሥርዓቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የማጥራት አቅምን በማሳደግ፣ በበጀት ዓመቱ የቀረቡ መዝገቦች ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ የፋይሎችን መጨናነቅ ማስቀረት መቻሉን አስረድተዋል።
ጉዳዮችን በተቀመጠው የጊዜ ስታንዳርድ ውስጥ የመወሰን አቅምን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ ውጤታማ እንደነበርም ተናግረዋል።
የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት የኦዲት ጥራትና ተደራሽነትን በማሳደግ ረገድ የተሻሉ ተግባራትን ማከናወኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ዋና ኦዲተር አቶ አስራት አበበ ናቸው።
ከክልሉ ምክር ቤት ኦዲት አስመላሽ ግብረ ኃይል ጋር በመቀናጀት በተሰራው ስራ የኦዲት ማስመለስ ሥራውን ከ70 በመቶ በላይ ማድረስ እንደተቻለ ገልጸው በክዋኔ ኦዲት ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ምክር ቤቱና አስፈጻሚ አካላት በቅንጅት በሠሩት ሥራ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል፣ የሥራ ዕድልን ከግብርና ሜካናይዜሽን ጋር ማያያዝ፣ እንዲሁም በኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ያልተጠናቀቁ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማጠናቀቅን ጨምሮ፣ የገቢ አማራጮችን ማስፋፋት ላይ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መጠናከር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ የቀረበውን ሪፖርት ተወያይቶ በማፅደቅ ሲያካሂድ የቆየውን 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን ለምክር ቤት አባላት ዕውቅና በመስጠት አጠናቋል።