ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት በዘላቂነት ራሱን ለመቻል የፋይናንስ ነጻነትና መዋቅራዊ ሪፎርም ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቷን ችግሮች በራሱ የሚፈታና የልማት አጀንዳዎቹን በውጤታማነት የሚያስፈጽም እንዲሆን የፋይናንስ ነጻነትን ማረጋገጥና የመዋቅራዊ ሪፎርም ሂደቶችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

49ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በዚህ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስብሰባው በህብረቱ በጀት፣ በፋይናንስ ራስን መቻል፣ በመዋቅራዊ ሪፎርምና በሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት በራሱ አቅም የሚመራና የአህጉሪቱን የልማት አጀንዳዎች በውጤታማነት የሚያስፈጽም እንዲሆን አባል ሀገራት የህብረቱን በጀት በራሳቸው አቅም የመሸፈን ቁርጠኝነት ሊያሳዩ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸውን አስታውሰዋል።

አፍሪካ በሰላምና ደህንነት፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት በርካታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህን በውጤታማነት ለማስፈጸም የአፍሪካ ህብረት በፋይናንስ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ተቋም መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች አህጉር መሆኗን በመጥቀስም፣ ሀብቷን ለጋራ ጥቅም ለማዋል በትብብርና በጋራ አሰራር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት አምባሳደር ነብያት፤ ይህም በኢትዮጵያ የቀረበ ቁልፍ መልዕክት መሆኑን ጠቁመዋል።

በስብሰባው በበጀት፣ በፋይናንስ ራስን መቻልና በመዋቅራዊ ሪፎርም ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች የህብረቱን የገንዘብ አቅም የሚያጠናክሩ ዘላቂ የፋይናንስ መሰረት የሚፈጥሩ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

አምባሳደር ነብያት አክለው እንደገለጹት፣ አጀንዳ 2063 የአፍሪካ ህብረት የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ሲሆን፣ የሰላምና ደህንነት፣ የሰዎች ነጻ እንቅስቃሴ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች አህጉራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችን ያካተተ ነው ብለዋል።

የልማት አጀንዳዎቹ በአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎች እየተገመገሙ የአፈጻጸም ሂደታቸውንም በቀጣይነት የሚከታተለው መሆኑን ጠቁመው፤ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ ከሚያጸድቃቸው ምክረ ሀሳቦች በመነሳት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ገልጸዋል።

አፍሪካ ሙሉ ነጻነቷን ለማረጋገጥ የኢኮኖሚ ነጻነት እውን መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለዚህም አባል ሀገራት የጋራ ተቋማቸው ለሆነው የአፍሪካ ህብረት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስና የራሱን አጀንዳዎች በራሱ አቅም የሚያስፈጽም ተቋም እንዲሆን የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አምባሳደር ነብያት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም