ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከል ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከል ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው
አምቦ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ) :-የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ሀገር በቀል ዛፎችንና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ባካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የማኅበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባይሳ ለታ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ተግባሩ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን እያሳለጠ ይገኛል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ሀገር በቀል ዛፎችንና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በራሱ ችግኝ ጣቢያዎች ያዘጋጃቸውን የተለያዩ ችግኞች ከመትከል ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ ሲያቀርብ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ዛሬ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በጉደር ማሞ መዘመር ካምፓስ በመገኘትና ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራውን ማኖሩን ተናግረዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ብዙነሽ ሚደቅሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በራሱ ማዕከል ዝርያቸው እየተመናመኑ የመጡ ሀገር በቀል ዛፎችን በምርምር እያባዛ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከምርምር ማዕከሉ የወጡትን ችግኞች ለአካባቢው ማኅበረሰብ በማቅረብ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በተሻለ ሁኔታ እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞች የፓፓያ፣ የአቮካዶ፣ የሙዝ እና የሌሎች ፍራፍሬዎች ዝርያዎች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የጉደር ማሞ መዘመር ካምፓስ ዋና ዳይሬክተር ንጉሤ በቀለ (ዶ/ር) ናቸው።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የተተከሉ ችግኞችን በማረም፣ በመኮትኮትና በመጠበቅ ውብና ጽዱ የሆነች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ የዜግነት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።