ቀጥታ፡

የጥበብ ዘርፉን አበርክቶ የሚያጎሉ ስራዎችን በጥናትና ምርምር የማገዝ ተግባር እየተከናወነ ነው

ባህር ዳር፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥበብ ዘርፉን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለውን አበርክቶ ለማጉላት የሚያስችሉ ስራዎችን በጥናትና ምርምር የማገዝ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለፀ።

በዘርፉ የሚሰማሩ ወጣት ሴቶች እያጋጠማቸው ባለው ተግዳሮትና መፍትሔ አመላካች ጥናትና ምርምር ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ተካሄዷል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ የጥበብ ዘርፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለውን የላቀ አበርክቶ በአግባቡ መጠቀም ይገባል። 

በዚህም ጥበብ ከመዝናኛነት ባለፈ የማኅበረሰብ ግንኙነትን በማጠናከር ለሰላም ግንባታና ለዘላቂ ልማት ለማዋል እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በተለይም የኪነ-ጥበብ እና ዕደ-ጥበብ ዘርፉ ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል ፈጠራ እያገዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም ዘርፉን በጥናትና ምርምር በማገዝ በኩል ክፍተት እንደነበረ አንስተው፤ አሁን ላይ አበርክቶውን የበለጠ ለማሳደግ መንግሥት በሰጠው ትኩረት መሠረት በምርምር ታግዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 


 

በተለይም ወጣት ሴት የጥበብ ባለሙያዎች ወደ ጥበብ ዘርፉ ለመግባትና ከገቡ በኋላም በሙያው የመዝለቅ ችግር እንደሚስተዋል አመልክተዋል።

በመሆኑም የተጠቀሱትንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ የፈጠራ አቅማቸውን በመጠቀም የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው የማድረግ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዚህም የጥበብ ዘርፉ ኢኮኖሚውን በዘላቂነት መደገፍ እንዲችል በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ አንስተው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ብሎም የጥናት ፕሮጀክቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ በበኩላቸው፤ በሀገራችን በዘርፉ የሚሰማሩ ወጣት ሴቶች የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠማቸው መሆኑ በተደረገው ጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል። 

በዚህም በቤተሰብም ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ በሚስተዋል ያልተገባ ጫና በዘርፉ የሚሳተፉ ሴቶች ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ ማደግ እንዳልቻለ አንስተዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ ጥናት መካሄዱን አንስተው፤ ጥናቱ በአምስት ክልሎች 500 የሚደርሱ ተሳታፊዎችን በመድረስ የተዘጋጀ መሆኑን አክለዋል። 

በሦስት ዓመታት በተካሄደው ጥናትም 13 ተመራማሪዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ የጥናት ውጤቱም ለፖሊሲ አውጪዎች ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል። 

ጥናቱ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆንም ሚዲያውን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።

በመድረኩ የክልል አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የጥበብ ሰዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም