ቀጥታ፡

ዲሞክራሲን ለማፅናትና የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦ ዲሞክራሲን ለማፅናትና የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙ ስኬታማ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።

በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት አቶ ጌቱ ወዬሳ እንዳሉት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ፓርቲውን በአሰራር፣ በሰው ሀይል እና በአደረጃጀት የማጠናከር ስራ ተሰርቷል።

በበጀት አመቱ ዲሞክራሲን ለማፅናት መሰረት የጣሉ ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።

ገዥ ትርክትን በመገንባት ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ አዎንታዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በተሻለ አፈጻጸም እንዲተገበር በቅንጅት፣ በተጠያቂነትና በውጤት ተኮር አሰራር መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ስራዎችን በማቀናጀት በተለይም የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት፣ የገበያ መረጋጋትን በማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

እንዲሁም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ስራዎች እንደሚሰሩም አብራርተዋል።

በተለይም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት ጋር የቅንጅት ስራዎች በማስቀጠል ስኬቶችን የበለጠ ማላቅ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

የተጀመሩ የንቅናቄ ስራዎች ባህል እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማጠናከር ስራም መጠናከር አለበት ነው ያሉት።

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት እየተደረጉ የሚገኙ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

“አዲሱ በጀት ዓመት ህዝቡን ይበልጥ የምናገለግልበት፣ ክልሉን የብልፅግና ተምሳሌት የሚያደርጉ ስራዎችን አጠናክረን ለማስቀጠል የክትትልና ድጋፍ ተግባራት የሚጠናከሩበት ይሆናል” ሲሉም ገልጸዋል።

የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነትና በከፍተኛ ትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም