በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች ለከተማዋ ዕድገት ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች ለከተማዋ ዕድገት ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ በወልቂጤ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የከተማዋን ዕድገት እያፈጠኑ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገለጹ።
በከተማው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትእና የድልድይ ግንባታዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በዘላቂነት የሚመልሱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ነው ያስታወቀው ።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ነው።
በከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ዝርጋታ፣ጤናና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የበርካታ መሰረተ ልማቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የነዋሪውን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት ከመመለስ ባለፈ የከተማዋን ዕድገት እያፈጠኑ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት ።
ይህም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማጠናከር ከተማዋን ተመራጭ እያደረጋት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ ሙራድ ለበርካቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል ።
ለአገልግሎት የበቁትን ጨምሮ አስተዳደሩ የሚቀርቡ የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ለማረጋገጥ እንዲቻል የተሻለ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዞኑ በ2018 በጀት አመት በህብረተሰብ ተሳትፎ በተገኘ ከ620 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልና አዳዲስ ግንባታዎች ማከናወን መቻሉንም ነው የገለጹት።
ይህም ለመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ ኑርድዋን ዱላ እና ወይዘሮ አነኋት ያሰና በበኩላቸው ፤ነዋሪው ለረጅም ጊዜ ሲነሳቸው የነበሩ የመንገድ እና ሌሎችም መሰረተ ልማት ጥያቄዎች በመመለሳቸው ተጠቃሚ አድርጎናል ነው የሚሉት።
አስተዳደሩ ህዝቡ የሚያቀርባቸውን የልማት ጥያቄዎች በማዳመጥ እየሰጠ ያለው ምላሽ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የተናገሩት።
ለአብነትም በአካባቢው ለረዥም ጊዜ ሲቀርብ ለነበረው የድልድይ ግንባታ ፈጣን ምላሸ መሰጠቱ በውሃ ሙላት ምክንያት ይጠፋ የነበረው የሰው ህይወትን በማስቀረት እፎይታን የሰጠ እንደሆነም አመልክተዋል።