የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ማህበረሰባዊ እሴትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ማህበረሰባዊ እሴትን እያሳደገ ነው
ሰመራ፣ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፡- የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ማህበረሰባዊ እሴትን ለማሳደግ ማገዙን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሰላም ሚኒስቴር ከአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር "በጎነት ለአብሮነት"በሚል መሪ ሐሳብ የሰላም የክረምት የበጎ ፍቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል።
በዕለቱ የተገኙት በሰላም ሚኒስቴር የሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አሰፈፃሚ ዘቢባ የሱፍ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ በሰላም የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የአንድነትና የአብሮነት ማህበራዊ አሴቶችን ለማጠናከር እየሰራ ነው።
የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ተሳትፎን በማጠናከር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በዘንድሮው መርሃ ግብር 6 ሺህ ያህል ወጣቶች የሚሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
በተግባሩም የቤት ዕድሳት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የከተሞች ፅዳትና ውበት፣ የተማሪዎች ትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እና የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሁም የምግብና የአልባሳት ድጋፍ የሚከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም 10 ሚሊየን የማህበረሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
መርሃ ግብሩ ሀገር ወዳድ መልካም ስነ ምግባር ያለው ትውልድ ለማስቀጠል ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ቢላል ዳርጌ በበኩላቸው እንዳሉት መርሃ ግብሩ ከተጀመረ አንስቶ አዎንታዊ ለውጦች ታይተዋል።
በዚህም የመረዳዳትና የአብሮነት ባህልን በማጠናከር የአካባቢያችንን ሰላምና ደህንነት ማስቀጠል ላይ መሰራቱን ገልፀዋል።
ተግባሩ በአፋር ክልል ደረጃ በሠመራ ሎጊያና አዋሽ ሰባት ከተሞች በዛሬው ዕለት መጀመሩን ተናግረዋል።
የሰመራ ሎጊያ በጎ አድራጎት ወጣቶች ሰብሳቢ ወጣት መሐመድ ዓሊ እንደተናገረው ወጣቶች በጎ ስራ በመስራታቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ ኑር ሳሊምና የተለያዩ አደረጃጀቶች ተወካዮች በተገኙት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከናውኗል።