ቀጥታ፡

በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችሉ ዲጂታል መተግበሪያዎች ገቢራዊ ተደርገዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦በነዳጅና ኢነርጂ ዘርፍ በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችሉ ዲጂታል መተግበሪያዎች ገቢራዊ መደረጋቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ግብይቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት መቆጣጠር የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን አስመርቋል፡፡


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋማትን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በማደራጀት ምቹ የሥራ ከባቢና ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋት ይገባል፡፡

ዘመኑን የዋጀ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሠራር ሥርዓት ለተቋማዊ ግንባታ የጎላ ሚና እንዳለው በመግለጽ፤ የዲጂታል አሠራር ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ዘርፉን አሠራር ይበልጥ ማዘመንና ግልጽነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ተመርቀው ሥራ ላይ የሚውሉት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የላቀና ቀልጣፋ አገልግሎት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ገቢራዊ የተደረጉት የዲጂታል መተግበሪያዎች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል መሆናቸውን ገልጸው፤ ተቋማዊ አሠራርን በቴክኖሎጂ ማዘመን ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የነዳጅ ዘርፉን ብልሹ አሠራር በሕጋዊ የአሠራር ሥርዓት ከመቆጣጠር ባሻገር በዲጂታል ቴክኖሎጂ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተቀናጀ የነዳጅ ሥርዓት አበረታች ሥራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን የበለጠ ግልጽነትን ለማስፈን ከ300 በላይ ዝርዝርና 47 ጥቅል አገልግሎቶችን በዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የመንግሥት መሻትና የሕዝብ ፍላጎት የሚሳካው አገልግሎቶችን ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ መደገፍ ሲቻል መሆኑን በማንሳት፤ የዲጂታል መተግበሪያዎች የዚህ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ ያለማቸው የዲጂታል መተግበሪያዎች ለተቋም ግንባታ መሠረት ይጥላሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ለተጀመረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የነዳጅ አቅርቦት ግብይትና ሥርጭት የተቋማትን አቅም መገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ የዲጂታል መተግበሪያው በነዳጅ ዘርፍ 29 አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ፣ በኢነርጂ ዘርፍ 36 አገልግሎቶችን በከፊል በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስጠት ተጀምሯል ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም