ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አሰባሳቢና ገዥ ትርክት በመገንባት ህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነትን በማጽናት ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል-ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

ሮቤ፣ ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ አሰባሳቢና ገዥ ትርክት በመገንባት ህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነትን በማጽናት ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ 'ውጤታማ ተግባቦት ለጠንካራ ፓርቲ' በሚል መሪ ሀሳብ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዶች ላይ የሚመክር መድረክ በባሌ ሮቤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ አሰባሳቢና ገዥ ትርክት በመገንባት ህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነትን በማጽናት ረገድ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን አካታች፣አሳታፊና የሃሳብ ብዝሃነት የሚንሸራሸርበት በማድረግ እንዲሁም የዳበረ የዴሞክራሲ ስርአት በመገንባት ሂደት ጠንካራ መሰረት እያኖረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በፓርቲው አባላትና አመራሮች መካከል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት  እንዲሁም የገዥ ትርክት ግንባታ እንዲጠናከር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።


 

በተጨማሪም ከቤተሰብ ጀምሮ በሀገር ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ስለመከናወናቸው አንስተው በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ሲሉ ተናግረዋል።

አካታች፣ አቃፊና አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችሉ ተግባራት በህዝብ ግንኙነት ዘርፉና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መከናወናቸውንም አብራርተዋል።

"ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን ሀገር ለመለወጥ የተነሳ አይደለም" ያሉት ዶ/ር ቢቂላ፤ በሀገር ጉዳይ በመደመር እሳቤ አካታችና አሳታፊ የሆነ አዲስ የፖለቲካ እሳቤ እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።


 

በ2018 የበጀት ዓመት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መካሄዱም ትልቅ ሀገራዊ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

በምርጫው ህዝቡ ለብልጽግና ፓርቲ በሰጠው ይሁንታ መሰረት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት መንግሥት በመመስረት በላቀ መልኩ ህዝባዊ አደራውን ለመወጣት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በሚቀጥሉት አምስት አመታት ሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም