የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከዚምባብዌ እና ቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከዚምባብዌ እና ቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ) ፦የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ከሚገኘው 49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን ከዚምባብዌ አቻቸው ከፕሮፌሰር አሞን ሙርዊራ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ ጠንካራ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው እና በአፍሪካ ሕብረት፣ በፓንአፍሪካኒዝምና በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ ምልከታ እንዳላቸው በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች የተለዋወጧቸው የትብብር ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማካሄድ ተስማምተዋል።
በተመሳሳይ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቤኒን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሪን አሞሪ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ሚኒስትሮቹ ሁለቱ ሀገራት ከአሁን በፊት የተፈራረሟቸውን ሥምምነቶች ወደ ተግባር በሚለውጡባቸው አግባቦች ዙሪያ ሐሳብ የተለዋወጡ ሲሆን፣ ቤኒን ከኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ልምድ ለመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ሚኒስትሯ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።