በሰሜን ሸዋ ዞን ከ177ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን ከ177ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል
ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 21/ 2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው ክረምት ከ177 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ሁሉምታየ ዘነበ እንደገለፁት፤ በዚህም በ2018/19 የመኸር ምርት ዘመን 563 ሺህ 336 ሄክታር መሬት በሰብል ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ባጠቃላይ ከሚለማው ማሳ ውስጥም ከ308 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በመጠቀም በጤፍ ፣ ስንዴ ፣ ማሽላ፣ በቄላና ማሾ ሰብሎች ለማልማት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አስካሁን በተደረገው ጥረትም 196 ሺህ 417 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ177 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።
የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎችም አርሶ አደሩ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን፣ሌሎች የተሻሻሉ አሰራሮችንና ግብአትን ተጠቅመው በመዝራት ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም ዝናቡ ዘግይቶ በጣለባቸው አካባቢዎች ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲዘራና በማሳው ዳር እና ዳር ውሃን አቅቦ የሚያቆይ ጉድጓድ በመቆፈር እንዲጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ የሞረትና ጅሩ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት መዝገቡ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስድስት ሄክታር መሬታቸውን በኩታ ገጠም በማረስ በስንዴ፣በጤፍና በጥራጥሬ ሰብሎች ሸፍነዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቡቃያውን መንከባከብ መጀመራቸውን ነው የተናገሩት።
ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ማሙሽ በቀለ በበኩላቸው፤ያለው የዝናብ ስርጭት ጥሩ በመሆኑ ሶስት ሄክታር መሬታቸውን በሰንዴ ሰብል መሸፈን መቻላቸውን አስረድተዋል።
ምርታማነታቸውን ለማሳደግም የሚያስፈልጋቸውን ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን በወቅቱ ማግኘት በመቻላቸው ፈጥነው ወደ ዘር ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ከመኸር እርሻ 20 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።