ቀጥታ፡

በክልሉ የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል

ሚዛን አማን፣ ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቡና ልማትን በማስፋፋትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከፍ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን  የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጁአብ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ከቡና የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግ ልማቱን የማስፋፋትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ  ትኩረት ተሰጥቷል።


 

በዚህም በክረምቱ ወራት ከ25 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን ለመትከል ወደስራ መገባቱን ተናግረዋል።

የቡና ልማቱን  ለማሳካት ዝርያቸው የተሻሻሉና  ለደጋና ቆላማ አየር ንብረት  ተስማሚነታቸው በምርምር  የተረጋገጡ ችግኞች ለአርሶ አደሩ  መሰራጨታቸውን  ጠቁመዋል።

የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችም  በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለምርት የሚደርሱ እና ከነባሩ የቡና ዝርያ በእጥፍ  ምርት የሚሰጡ  መሆናቸውን  ጠቅሰው ልማቱን  ለማሳካትም ሙያዊ  ድጋፋና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሸካ ዞን የየኪ ወረዳ አርሶ አደር ሰሎሞን ብርሃኔ ከቡና የሚያገኙትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያላቸውን የቡና ማሳ በየዓመቱ እያስፋፉ መሆኑን ገልጸዋል።

አምና ከወረዳው ያገኙትን አንድ ሺህ  "ኬ1" የተሰኘ ምርጥ የቡና ችግኝ መትከላቸውንና ዘንድሮም ተግባሩን በማስቀጠል  አንድ  ሺህ ችግኞችን ለመትከል  እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ነባሩን  የቡና ዝርያ  በምርምር በተገኙ የቡና ዝርያዎች  እየተኩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ጢሞቴዎስ ከሮ እና ታደሰ እጅጉ ናቸው።

ቡናን ከማልማት ባሻገር ጥራቱን ለማስጠበቅ  በግብርና ባለሙያ ትምህርት ታግዘው እየሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ያላቸው ማሳ ላይ በየዓመቱ አዳዲስ ችግኞችን እየተከሉ የቡና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 614 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና እየለማ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም