ቀጥታ፡

ዘመናዊ የመሬት አያያዝ እና አስተዳደር ለጠንካራ ኢኮኖሚ ግንባታ ሚናውን እየተወጣ ነው

ጅማ ፤ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ዘመናዊ  የመሬት አያያዝ እና አስተዳደር አገልግሎት ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተገለጸ።

በጅማ ከተማ በዛሬዉ ዕለት የገጠር ካዳስተር ስፍር የመዝጊያ ፕሮግራም ተካሂዷል።


 

በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ በብልፅግና ፓርቲ  የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ነመራ ቡሊ ፣ የኦሮሚያ መሬት ቢሮ ሀላፊ መሠረት አሰፋ እና ሌሎችም የዞን እና የወረዳ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ነመራ ቡሊ በወቅቱ እንደገለጹት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ የመሬት አስተዳደር ትልቅ ሚና አለው።

ይህንን ከግብ ለማድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ነው  ብለዋል።

በክልሉ የተሰራው የካዳስተር ስራም ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።

ዘመናዊ  የመሬት አያያዝ እና አስተዳደር አገልግሎትን በማሳካት  ወደ ትልቅ የገቢ ምንጭ የመቀየር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።


 

የኦሮሚያ መሬት ቢሮ ሀላፊ መሠረት አሰፋ በበኩላቸዉ የመሬት ካዳስተር አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን አስገኝቷል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ አርሶ አደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት ማሸጋገር ፣ የመሬት ብክነትን ማስቀረትና ግልፅና ቀልጣፋ አገልግሎትን መስጠት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

በክልሉ በ21 ዞኖች ለ4 ሚሊዮን 69 ሺህ 179 አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን አስታውቀዋል።


 

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው የካዳስተር አገልግሎት የዞኑን ገቢ ከማሳደግ በተጨማሪ ኢንቨስትመንትን እያጠናከረ ነዉ ብለዋል።

ግልፅነትን በማስፈን ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ያስቻለ መሆኑንም አመልክተዋል።

የጅማ ዞን መሬት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አብዱልሀሚድ ሀጂ በዞኑ የተጀመረዉ የመሬት ካዳስተር አገልግሎት በርካታ ጠቀሜታ ማስገኘቱን ጠቁመው በ20 ወረዳዎች እና በ513 ቀበሌዎች መሬት በካዳስተር መሰፈሩን ተናግረዋል።

በዚህም ለ397 ሺህ 647 አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን ገልፀዋል።

የካዳስተር አገልግሎት የአርሶ አደሩን የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር በማሻሻል ግንዛቤን ማሳደጉንም አክለዋል።


 

በጅማ ዞን የሰኮሩ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዝናብ አባ ጎጀም ሁለት ሄክታር መሬታቸዉ ተሰፍሮ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታቸዉን ተናግረዉ አገልግሎቱ መሬታቸውን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዳገዛቸዉ ጠቅሰዋል።


 

ሌላዉ የሊሙ ሰቃ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ፋሪስ መሀሙድ መሬት ወደ ካዳስተር መግባቱ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸዉ በባለቤትነት ዙሪያ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን መፍታቱን ገልፀዉ የይዞታ ማረጋገጫ በማግኘቴ ተደስቻለሁ ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም