ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በዘላቂነት ለማስቀጠል ችግኞችን መንከባከብ ይገባል

ቃሉ ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያስገኝ ያለውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዘላቂ ለማድረግ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የክልሉ ግብርና ቢሮ አሳሰበ።

የደቡብ ወሎ ዞን የዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በቃሉ ወረዳ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።


 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው  በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በክልሉ  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአርሶ አደሩን  ምርታማነት ለማሳደግ እና ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ የማይተካ ድርሻ እያበረከተ ነው።

መርሃ- ግብሩ የደን ሽፋንን ለማሳደግና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ እያስገኝ ያለውን ጠቀሜታ ዘላቂ ለማድረግም በ260 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞች  እየተተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅትም የተተከሉ ችግኞችን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግም ህብረተሰቡ የእንክብካቤ ስራው ላይም  ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው፣ በዞኑ 40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 230 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተገኙ ውጤቶችን  በተጨባጭ  በመገንዘቡ የፍራፍሬ ችግኝን በስፋት እየተከለ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የችግኝ ተከላ ስራው በተፋሰሶች፣ በወል መሬቶች፣ በአርሶ አደሩ ማሳና በሌሎች ቦታዎች በስፋት እየተካሔደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በየዓመቱ የተተከሉት ችግኞች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ በመሆናቸው የእንክብካቤ ሰራ ላይ እንደሚሳተፉ ያነሱት ደግም የቃሉ ወረዳ 019 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሀዋ እንድሪስ ናቸው።

ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በፍራፍሬ ችግኝ በመሸፈንም ከልማቱ እያገኙ ያለውን ጥቅም ለማሳደግ በትጋት እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጡት።


 

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርታማነትን ለማሳደግና የእንስሳት መኖን በበቂ ሁኔታ ለማግኝት እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።

በማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም