አፍሪካ ከውጭ የፋይናንስ ጥገኝነት በመላቀቅ የውስጥ የገቢ አቅሟን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅባታል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ ከውጭ የፋይናንስ ጥገኝነት በመላቀቅ የውስጥ የገቢ አቅሟን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅባታል
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ዘላቂ ልማቷን ለማረጋገጥ ከውጭ የፋይናንስ ጥገኝነት ተላቃ የውስጥ የገቢ አቅሟን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ ክሌቨር ጋቴቴ ገለጹ።
49ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የምክር ቤቱ ስብሰባ “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚለው የ2026 የህብረቱ ዓመታዊ መሪ ሀሳብ አማካኝነት ይከናወናል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ኤድዋርድ ቢዚማና፣ የአባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች እንግዶች በስብሰባው መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ ክሌቨር ጋቴቴ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የጂኦፖለቲካ ውጥረቶች፣ የግጭቶች መበራከት፣ የብድር ክፍያ ጫና እና የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት በአህጉሪቷ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።
እነዚህን ፈተናዎች ለመወጣት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አባል ሀገራት የታክስ ስርዓታቸውን እንዲያዘምኑ ጠቁመው፤ ኮሚሽኑ የሀገር ውስጥ ካፒታል ገበያዎችን እንዲያጠናክሩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
አህጉሪቷ በየዓመቱ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ሳቢያ በርካታ ገንዘብ እንደምታጣና የታክስ መሰብሰብ አቅሟም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ 16 በመቶ ብቻ መሆኑን አመልክተው፤ ይህ አሰራር በአስቸኳይ መለወጥ እንዳለበትም ተናግረዋል።
በግብርና፣ በኃይል፣ በኢንዱስትሪ እና በአየር ንብረት መከላከል የተቀናጀ ፖሊሲና አሰራር መከተል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለአህጉሪቱ ልማት ማዋል እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ማሸሽን መግታት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ እርስ በርስ ንግድ 17 በመቶ ብቻ ሲሆን፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሙሉ በሙሉ ሲተገበር በ2045 የውስጥ ንግድን እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የመረጃ ስርዓቶችን ለማዘመንና ዲጂታል መሠረተ-ልማቶችን ለማስፋፋት መዋዕለ-ነዋይ ማፍሰስ እንደሚገባም ገልጸዋል።