አፍሪካ አጀንዳዎቿን ለማስፈጸም የራሷን ሀብት መጠቀም ላይ ትኩረት ማድረግ አለባት - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ አጀንዳዎቿን ለማስፈጸም የራሷን ሀብት መጠቀም ላይ ትኩረት ማድረግ አለባት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ አጀንዳዎቿን ለማስፈጸምና ግቦቿን ለማሳካት የራሷን ሀብት መጠቀም ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባት የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሰብሳቢ ኤድዋርድ ቢዚማና ገለጹ።
49ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ስብሰባው እየተደረገ ያለው “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ሰብሳቢ ኤድዋርድ ቢዚማና አፍሪካ በጋራ ጉዳዮቿ ላይ በአንድ ድምፅና በተባበረ ክንድ መቆም እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ሚኒስትሩ አፍሪካውያን ሁለንተናዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ በፓን-አፍሪካኒዝም እሴቶች ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የጋራ አንድነት መገንባት አለባት ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የጋራ አቋም የያዙባቸውና የህብረቱ ማዕቀፎች በሚገባ መተግበርና አፈጻጸማቸውን መከታተል እንደሚገባም አመልክተዋል።
ማዕቀፎቹ የአፍሪካን ፍላጎት በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስከበር ዋና መደላድል መሆናቸውን ነው የገለጹት።
የህብረቱን ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ በተመለከተ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ አፍሪካ የራሷን አጀንዳዎች ለማስፈጸምና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ነፃነቷን ለማስጠበቅ የራሷን ሀብት መጠቀም ላይ ትኩረት ማድረግ አለባት ብለዋል ሚኒስትሩ።
በዚህ ረገድም የአፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ ድጋፋቸውን ማድረግ እንዳለባቸው ነው ጨምረው የተናገሩት።
ስምምነት እና መግባባት (Consensus) የፖለቲካ ብስለት እንጂ የድክመት ምልክት እንዳልሆነ ጠቁመው ይህም የአፍሪካ ሀገራትን የሚያቀራርቧቸውን የጋራ እሴቶች እንዲፈልጉ የሚያስችል ዋና መሳሪ ነው ብለዋል።
የተያዙ አጀንዳዎችንና የተገቡ ቃል ኪዳኖችን ለአፍሪካውያን ህይወት ለውጥ ወደሚያመጡ ተጨባጭ ውጤቶች መቀየር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።