በጉራጌ ዞን በፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን በፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው
ወልቂጤ ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ በፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመም ልማት ላይ መሰማራታችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ አስችሎናል ሲሉ የጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በዞኑ የአበሽጌ እና የቸሃ ወረዳ አርሶ አደሮች፤ከእንሰት እና ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመም ልማት ላይ በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የአበሽጌ ወረዳ አርሶ አደር ዳዊት አሰፋ ፤ በግብርና ባለሙያዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ ቅመማ ቅመም ማምረት መጀመራቸውን ገልፀዋል።
በአካባቢው ከእንሰት እና ሰብል ልማት ባለፈ የቅመማ ቅመም ልማት ብዙም ያልተለመደ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ በፍራፍሬ ልማት ላይ በመሳተፍም ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ሞሳ ጀማል፤ላለፉት አራት አመታት የተለያዩ የፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመምን በማምረት ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
የተሰማሩበትን የፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት ስራ ውጤታማ ለማድረግም በዘርፉ ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን ልምድ ከመውሰድ ባለፈ የባለሙያዎች ድጋፍንም ተግባራዊ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በፍራፍሬ እና በአትክልት ልማት ላይ በመሰማራት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን የተናገሩት ደግሞ የቸሃ ወረዳ አርሶ አደር ዲሮ በድር ናቸው፡፡
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደገለጹት ፤ በዞኑ የፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ ናቸው።
በተለይ በአቮካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎ ፣ አናናስ እና ፓፓያ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል።
በዞኑ ፍራፍሬና አትክልትን በስፋት ከማልማት በተጨማሪ በቅመማ ቅመም ልማት ላይ በማተኮር ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ አመት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የተሻሻሉ የአቮካዶ፤ የፓፓያ እና የተለያዩ ፍራፍሬ ችግኞች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
ልማቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ለአርሶ አደሩ ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ የባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡