ቀጥታ፡

አካታችና አሳታፊ የሆነው ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ አቅም ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ አካታችና አሳታፊ የሆነው ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ስምንት የምክክር አጀንዳዎችን በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

ሁሉንም አሳታፊ ያደረገው ይህ የምክክር መድረክ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመመካከር መፍትሄ ለማበጀት ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኗል።

ተመካካሪ አቶ ተስፋዬ ያዴሳ እንደገለጹት፤ የምክክር መድረኩ ሁሉንም ያሳተፈና አካታች በመሆኑ በጋራ መግባባት ሀገርን ማስቀጠል እንደምንችል ያየንበት አጋጣሚ ነው፡፡

ቀደም ሲል ልንግባባባቸው ያልቻልናቸውን ነገሮች በሰፊው እየተወያየንባቸውና እየተግባባንባቸው እንገኛለን ያሉ ሲሆን፤ ምክክሩ ሀሳባችንንና የማህበረሰባችንን ፍላጎት ያለምንም ገደብ በነጻነት እንድንገልጽ ሰፊ እድል ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡

ምክክሩ ውስጣዊ ስሜታችንንና አመለካከታችንን ያለምንም ገደብ እንድንገልጽ ዕድል የፈጠረና ተስፋ ሰጪ ሂደት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተመካካሪ ሙሉነሽ ዋቅቶላ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ክልሎች ባለፈ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ ነው።

የምክክር መድረኩ አሳታፊነትና አካታችነት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ ሳሙኤል ብርሀኑ፤ ሀገራዊ ምክክሩ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁሞ፤ ለዘመናት ስር የሰደዱ ችግሮችን በመመካከር መፍታት የሚያስችል እንደሆነም ተናግሯል፡፡

የምክክር መድረኩ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በአንድነትና በግልጽነት ተነጋግረው እንዲተማመኑ በማድረግ ለሀገራችን ዘላቂነት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ያሉት ደግሞ ተመካካሪ በየነ ሶሎ ናቸው።

ሁሉንም በአንድ ልብ ያቀራረበና ወደ ዘላቂ መፍትሔ የሚያሸጋግር ምክክር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም