ቀጥታ፡

አፍሪካ የራሷን ዘላቂና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ በመገንባት ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን ማጎልበት አለባት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ አፍሪካ የራሷን ዘላቂና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ በመገንባት ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነቷንና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ማጎልበት እንዳለባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ "የአፍሪካ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓት ማንበር" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የጂኦፖለቲካ ውድድር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች በዓለም አቀፍ ሥርዓት ላይ ለውጥ እያመጡ ነው።

አፍሪካ የዓለምን ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሁነቱን በራሷ መንገድ መቅረጽ እንዳለባትም ገልጸዋል።

ለዚህም አህጉራዊ ተቋማት የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ ሪፎርሞችን ማድረግ እንዳባቸው ነው የተናገሩት።

ሕብረቱም በቴክኒካዊና ጥቂት ማስተካከያዎች ላይ ብቻ ሳይወሰን ስትራቴጂክና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ያካተተ ጥልቅ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

አፍሪካ ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነቷንና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ለማሳደግ የራሷን ዘላቂና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ሊኖራት ይገባል ብለዋል።

በዚህም አፍሪካ ለዓለም አቀፍ ችግሮች አህጉራዊ መፍትሔን በማበጀት ቁልፍ ተዋናይ መሆን እንደሚጠበቅባት ገልጸዋል።

አፍሪካ በሚያጋጥሟት ፈተናዎች መሀል ዕድገት እያስመዘገበች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በ2026 ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ 10 የዓለም ሀገራት መካከል ስምንቱ አፍሪካውያን እንደሚሆኑ ይጠበቃል ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ውሳኔዎቹን ማስፈጸም የሚያስችለውን ሪፎርም በማድረግ ዘላቂና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ሊኖረው እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።


 

የአፍሪካ ሃብቶች በአህጉሪቱ ተቋማትና ማዕቀፎች መመራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትን የአህጉራዊ አንድነትና የጋራ ራዕይ ዋነኛ ተቋም አድርጋ ትመለከታለች ብለዋል።

ለሕብረቱ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዘላቂ ግቦች መሳካት በትኩረት እንደምትሰራም አስገንዝበዋል።

የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት በአፍሪካ ሕብረት የ2026 የዓመቱ መሪ ሀሳብ ትግበራና አፈጻጸም ላይ በቀረበው ሪፖርት ላይ በጥልቀት ይመክራል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረት ስምምነቶች በፍጥነት በሚጸድቁበትና በሚተገበሩባቸው ጉዳዮች እንዲሁም በአጀንዳ 2063 ትግበራ ዙሪያ በቀረበው የኮሚቴው ሪፖርት ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም