ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር ግንባታና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሠረት የሚጥል ነው - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ለሀገር ግንባታና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሠረት የሚጥል ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማወያየት ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአጀንዳዎቹ ላይም አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር እያደረጉ ይገኛሉ።

በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የሚያስችል ነው።

የምክክር ሂደቱ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ የድርሻውን የሚያበረክትበት አውድ የፈጠረ ሲሆን ተመካካሪዎች ለሀገር ግንባታ የሚረዱ ገንቢ ሀሳቦችን እያንሸራሸሩበት እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ተመካካሪ ኑር ሰይድ እንደገለጹት፣ ምክክሩ የተረጋጋች፣ ወደፊት ተሻጋሪና ለመጪው ትውልድ የምትሆን ሀገር መገንባት ያስችላል።

ባለፉት ቀናትም ምክክሩ የሁሉም አካላት ሀሳብ የተከበረበት፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁሉም ሰው በነጻነት የሚሳተፍበት፣ ሀሳቦችን አቅርቦ የጋራ መግባባት ላይ የሚደረስበት መሆኑንና ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር መልካም መሠረት የሚጣልበት ነው ብለዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ ሬድዋን አህመድ በበኩላቸው፣ ምክክሩ ለሀገር ሰላም መስፈን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል ያሳተፈ ነው ብለዋል።

ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶች በምክክር ሊፈቱ እንደሚችሉ ከምክክሩ የእስካሁን ሂደት መገንዘባቸውን አስታውቀዋል።

ሀገር በጦርነት ሳይሆን በምክክርና በተሻለ ሀሳብ ነው የምትገነባው በመሆኑን ሁሉም ወገን ይህን መድረክ ሀገርን በአንድነት ለመገንባት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

የመመካከር ባህል ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ደምሴ ስኳሬ ናቸው።

ምክክር እየተደረገባቸው የሚገኙ አጀንዳዎች ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የመነጩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ምክክሩ በነጻነት የሚነሱ ሀሳቦች ተሰባስበው የጋራ መግባባት ላይ እየተደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ በዜጎች ንቁ ተሳትፎ ሀገርን ለመገንባት የተፈጠረ ትልቅ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም