በደቡብ ወሎ ዞን ከ71 ሺህ 800 በላይ አርሶ አደሮች የሀይል አማራጭ ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን ከ71 ሺህ 800 በላይ አርሶ አደሮች የሀይል አማራጭ ተጠቃሚ ሆነዋል
ደሴ ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ወሎ ዞን ከ71 ሺህ 800 በላይ አርሶ አደሮችን በተለያዩ የኃይል አማራጮች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ጽጌ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በገጠራማ አካባቢ ተበታትኖ የሚኖረውን ማህበረሰብ በኃይል አማራጮች ተጠቃሚ በማድረግ ኑሮውን ለማዘመን ጥረት እየተደረገ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአማራጭ ሀይል ቴክኖሎጂን ለማስፋት በተደረገ ጥረት 71 ሺህ 840 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚሁ ወቅትም አንድ ሺህ 71 ባዮጋዝን በማስገንባት፣ 16 ሺህ 486 በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ሶላሮችና 54 ሺህ 283 የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች መሰራጨታቸውን ጠቁመዋል።
ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮችም ለማገዶ መሰብሰብና ግዥ ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ በመቆጠብ ለሌሎች የልማት ስራዎች ለማዋል እንዳስቻለው አስረድተዋል።
በተጨማሪም የማገዶ እንጨትን በመጠቀም በሴቶችና በህጻናት ላይ በጭስና በእሳት ቃጠሎ ይደርስ የነበረውን የጤና ችግሮች ለመቅረፍ ማስቻሉን አስገንዝበዋል።
በተለይም አርሶ አደሩ የባዮ ጋዝ ተረፈ ምርትን ለአፈር ማዳበሪያነት ለመጠቀም በመቻሉም ያወጣ የነበረውን ገንዘብ በመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዞኑ ኩታበር ወረዳ የ03 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፎዚያ ዳውድ በበኩላቸው፣ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ተጠቃሚ በመሆናቸው የስራ ጫና ከማቃለሉ ባለፈ አኗኗሯቸው እንዲሻሻል ማድረጉን ገልጸዋል።
ማገዶ ፍለጋ ይጓዙ የነበረውን ረዥም ርቀት ከማስቀረት ባለፈ በጭስ አማካኝነት ይፈጠር የነበረውን የጤና ችግርም እንዳስወገደላቸው ነው የገለጹት።
ሌላው የደሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ እሸቱ ፣ ባገኙት የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ምግብ ማብሰልና የመብራት አገልግሎት መጠቀም ጀምረዋል።
ቴክኖሎጂው ለማገዶ ፍለጋ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ከመቆጠብ ባለፈ ተረፈ ምርቱን ለማዳበሪያነት በመጠቀም የመሬት ለምነትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ከ56 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በተለያዩ የሀይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።