ቀጥታ፡

ግብርን በአግባቡና በወቅቱ በመክፈል የሚጠበቅብንን ሀገራዊ ግዴታ እየተወጣን ነው

ሀረር ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ ግብርን በአግባቡና በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን የሐረሪ ክልል ግብር ከፋዮች ተናገሩ።

የሐረሪ ክልል ታማኝ ለሆኑና ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል ላይ ላሉ  ነጋዴዎች እውቅና ሰጥቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ግብር ከፋዮች እንዳሉት ግብርን በአግባቡና በወቅቱ በመክፈል የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ግዴታ  እየተወጡ ነው።

ከክልሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች መካከል በአይን ህክምና ስራ ላይ የተሰማሩት  ዶክተር ኑረዲን አብዲ እንዳሉት፤ የሚጠበቅብኝን  ግብር በወቅቱ በመክፈሌ የተሰጠኝ እውቅና ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ ነው።

ከነጋዴው የሚሰበሰበው ግብር ለአካባቢው  ልማት መፋጠን የሚውል በመሆኑም ስራዎችን በማሳደግ ለሀገር እድገት ይበልጥ  አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚሰሩ ነው የገለጹት።

 ግብርን በአግባቡ መክፈል ለመጪው ትውልድ ምቹ የሆነች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥም የራስን አሻራ ለማኖር የማያስችል ነው ብለዋል።

በከተማው በሆቴል ስራ የተሰማሩት አቶ ሃይሉ ካሳ  እና ወይዘሮ ዩስራ መሀመድ  በበኩላቸው፤ ግብር መክፈል ለሀገር ልማትና እድገት  የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ የዜግነት ግዴታችን በመወጣት ላይ ነን ብለዋል።

በተለይም'' በአሁኑ ወቅት በሚካሔዱ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ በመሆናችን በወቅቱ በተገቢው መንገድ ወደንና ፈቅደን በሚፈለገው መንገድ ግብራችንን መክፈልን እንቀጥላለን''  ነው ያሉት።

በክልሉ መንግስት የተሰጣቸው እውቅናም ይበልጥ ለመስራትና ለሌሎች አርአያ ለመሆን እንዳነሳሳቸው አመልክተዋል፡፡


  

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ  እንደገለጹት፤ በክልሉ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የታክስ ተገዢነትን በማሳደግ የክልሉን የልማት ወጪ በራስ ገቢ ለመሸፈን በማቀድ ወደ ስራ ተገብቷል።

በተለይ የታክስ ህጎችን ወደ ስራ በማስገባት ፍትሃዊ የግብር ክፍያዎች እየተፈጸሙ  መሆኑን የገለጹ ሲሆን ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና ለውጥ እየተመዘገበበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት በክልሉ ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

በቀጣይም የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን የማዘመን እና የንግዱ ማሕበረሰብ በታክስ አሰባሰቡ ሒደት ላይ ግንዛቤውን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም