ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተከናውነዋል

ባህርዳር ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ በተጠናቀቀው በጀት አመት  የከተማውን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መከናወናቸውን የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለፁ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም በጀት አመት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፤ በከተማው በተጠናቀቀው በጀት አመት በሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል።

በሥራ እድል ፈጠራ፣ በኮሪደር ልማት፣ በቱሪዝም፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት  ውጤታማ ስራ መከናወኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋሲል አብዩ፣  በበጀት ዓመቱ ወጣቶችን በኢንተርፕራይዞች በማደራጀት  የስራ እድል  መፈጠሩን ጠቁመዋል። 


 

ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት  አገልግሎት አሰጣጡን  ፈጣን የማድረግና መሰረተ ልማት እንዲሟሉ  መደረጉን  ተናግረዋል።

​የመንግሥት አገልግሎትን ለማቀላጠፍም የአገልጋይነት መንፈስን በማጎልበትና የተቋማት አሰራርን በማሻሻል የተካሄደው የሪፎርም ሥራ መነቃቃት መፍጠሩን አውስተዋል።

በበጀት ዓመቱ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡንም ጠቅሰዋል።

​በቀጣይም የአመራሩን ተቀናጅቶ የመፈጸም አቅም በማሳደግ የተያዙ የልማት ግቦችን በማሳካት የከተማዋን ህዝብ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በተካሄደው የውይይት መድረክም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና የሁሉም የከተማ አስተዳደሩ መምሪያና ክፍለ ከተማ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም