የአፍሪካ ሀገራት የልማት ግቦችን የሚያሳኩ የአሰራር ማዕቀፎችን በፍጥነት ወደ ስራ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት የልማት ግቦችን የሚያሳኩ የአሰራር ማዕቀፎችን በፍጥነት ወደ ስራ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት አህጉራዊ የልማት ግቦችን እውን የሚያደርጉ ስምምነቶችን በአፋጣኝ አፅድቀው ወደ ትግበራ እንዲያስገቡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ጥሪ አቀረቡ።
49ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አፍሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ የሚመጡ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በሙሉ አቅሟ እየተጋፈጠች ነው።
የግጭቱ መቀስቀስ የዓለም አቀፍ የአቅርቦት መስመሮችን በማስተጓጎሉ ምክንያት የነዳጅ፣ የሸቀጣሸቀጥ እና የመሰረታዊ ቁሳቁሶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ማድረጉን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ጉዳዩን በጥልቀት ሲመረምሩት እንደቆዩና የዚህ ቀውስ ዳፋ ለበርካታ አመታት አብሮን ሊቆይ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በአህጉሪቱ እየተስፋፋ ያለው የሽብርተኝነት አደጋ እና የጤና ስጋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሊቀ መንበሩ አውስተዋል።
በሳህል ቀጣና ባደረጉት ጉብኝት የሰብአዊ ሁኔታዎችን መመልከትና ሽብርተኝነትን በጋራ መከላከል የሚያስችል ቀጣናዊ ትብብር ለማጠናከር ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (Africa CDC) እያከናወነ ላለው ስራ ላይ አባል ሀገራት ድጋፋቸውን እንዲያጠናከሩም ጠይቀዋል።
ሊቀ መንበሩ በአፍሪካ ህብረት የበጀት እና አደረጃጀት ላይ በሰጡት ማብራሪያም የ2027 የበጀት ረቂቅ 797 ሚሊየን 893 ሺህ 884 ዶላር መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
ይህ በጀት ከአባል ሀገራት መደበኛ መዋጮ እና በዓለም አቀፍ አጋሮች የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመዋል።
የአጀንዳ 2063 ሁለተኛውን የ10 ዓመት እቅድ ለማስፈጸም ወደ ሁለት ቢሊየን ዶላር ገደማ ፋይናንስ እንደሚያስፈልግ ነው ሊቀ መንበሩ ያስረዱት።
ኮሚሽኑ ለአፍሪካ ልማት የሚሆን የግል እና የህዝብ ካፒታልን መሳብ የሚያስችሉ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሚናውን እንደሚወጣም ተናግረዋል።
አባል ሀገራትም የህብረቱን የልማት ግቦች እውን ለማድረግ ቁልፍ የሆኑ ህጋዊ ስምምነቶችንና ሰነዶችን በፍጥነት እንዲያፀድቁ ጥሪ አቅርበዋል።