በክልሉ የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችል የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራርና ድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።
ከ300 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይም ለዚሁ ተግባር የሚውል የበቆሎ ልማት እየተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ኃይሉ ሀሰና እንደገለጹት፤ በክልሉ የሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመመከት የሚያስችል አቅም ለመገንባት እየተሰራ ነው።
በክልሉ አምስት ወረዳዎች ውስጥ የወል መሬትን በመጠቀም በቆሎ፣ ቦሎቄና ሌሎች ሰብሎችን በማምረት የመጠባበቂያ እህል ክምችት አቅምን የማሳደግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከ300 ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ በቆሎ እየለማ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከ12 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ ህብረተሰቡ በ"ካላሞ ፎጮ" ስርዓት እርስ በእርሱ የሚረዳዳበትን ባህል የማጎልበት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ይህም አርሶ አደሩ እህል በሚሰበሰብበት ጊዜ ከሚያገኘው ምርት ለወገኖቹ እንዲያጋራ በማድረግ የገንዘብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በዝናብ መስተጓጎል ምክንያት ማሳቸው የተጎዳባቸው አርሶ አደሮች የማካካሻ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ እንዲደርሳቸው መደረጉንም አክለዋል።
በክልሉ የደራራ ወረዳ አርሶ አደር በላይ ግዴሳ፤ በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ ካለሙት የበቆሎ ምርት ላይ በባህላዊ የመረዳጃ ስርዓቱ "ካላሞ ፎጮ" መሰረት እስከ አምስት ኪሎ ግራም ረዳት ለሌላቸው ወገኖች እንደሚለግሱ ገልጸዋል።
የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ ዲጋ በበኩላቸው፤ ከሚያገኙት የበቆሎ ምርት ላይ እስከ አምስት ኪሎ ግራም ለተቸገሩ ወገኖች መርጃ እንዲሆን በ"ካላሞ ፎጮ" በኩል እንደሚለግሱም ተናግረዋል።