ኤጀንሲው የጀመራቸውን የዲጂታል አሰራሮች አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው የጀመራቸውን የዲጂታል አሰራሮች አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የጀመራቸውን የዲጂታል አሰራሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡
የኤጀንሲውን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም አስመልክቶ ዋና ዳይሬክተሩ ዮሴፍ ንጉሤ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ኤጀንሲው በ2018 በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ተገልጋዮች 2 ነጥብ 4 ሚሊየን የኩነትና የነዋሪነት አገልግሎቶች መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የሞትና የጉዲፈቻ ምዝገባዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ወቅታዊ የኩነት ምዝገባ ለስታትስቲክስ፣ ለፖሊሲ ቀረጻና ለአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዜጎች የልደት ምዝገባቸውን በ90 ቀናት ውስጥ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ኤጀንሲው የኩነት ምዝገባ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በጤና ተቋማትና በፍርድ ቤቶች የአንድ መስኮት አሰራርን ማስፋቱን ገልጸዋል።
በዚህም 94 በመቶ የወቅታዊ የልደት ምዝገባዎች በጤና ተቋማት በተቋቋሙ የአንድ መስኮት ማዕከላት መከናወናቸውን፤ የፍቺና የጉዲፈቻ ምዝገባዎችም በፍርድ ቤቶች በተቀናጀ አገልግሎት 100 በመቶ መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ከአገልግሎት ዘመናዊነት አንጻርም ኤጀንሲው በአካል በመገኘት የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ ዲጂታል አሰራር ማሸጋገር መጀመሩን ጠቁመው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዚህም የልደት፣ የያላገባ ማስረጃና የመታወቂያ አገልግሎቶች ተገልጋዮች ወደ ቢሮ ሳይመጡ በዲጂታል ካሉበት ሆነው እንዲጠይቁ የሚያስችል ስርዓት መጀመሩን አስታውቀዋል።
ኦንላይን አገልግሎቱ ከተጀመረ በኋላ 8 ሺህ 872 ተገልጋዮች ወደ ቢሮ ሳይመጡ አገልግሎት ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የነዋሪነት መታወቂያን የማስተሳሰር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንና፤ ይህም የዜጎችን ማንነት በአንድ መለያ ለማረጋገጥና የሐሰተኛ ሰነዶችን አጠቃቀም ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 1 ሚሊየን 828 ሺህ 846 ተገልጋዮች በኤጀንሲው በኩል የፋይዳ ምዝገባ ማጠናቀቃቸውን፤ ፋይዳ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 8 ሚሊየን ያህል ተጠቃሚዎች በኤጀንሲው በኩል መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም 12 ሚሊየን የሚደርሱ የነዋሪነት ሰነዶች በዲጂታል ስርዓት እንዲቀመጡ መደረጋቸውን ገልጸው ይህም የሰነድ መጥፋትንና የመረጃ አያያዝ ችግሮችን በመቀነስ የአገልግሎት ጥራትን አሻሽሏል ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ወቅታዊ የኩነት ምዝገባ በተከታታይ እያደገ መምጣቱንና ይህም የአገልግሎቱ ተደራሽነትና ቅልጥፍና መሻሻሉን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
በ2019 በጀት ዓመት የሞት ምዝገባን ወደ ጤና ተቋማትና ሌሎች የማህበረሰብ ተቋማት ማስፋት፣ የመታወቂያ ህትመትን ወደ ወረዳ ማውረድና የኦንላይን አገልግሎቱን ማስፋት ዋና ዕቅዶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኤጀንሲው በ2018 በጀት ዓመት ባስመዘገበው የአገልግሎት አፈጻጸም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እውቅና እና ሽልማት ማግኘቱንም ገልጸዋል።