የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት የዜጎችን ህይወት እያሻሻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት የዜጎችን ህይወት እያሻሻለ ነው
ጅም ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት የዜጎችን ህይወት እያሻሻለ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ነመራ ቡሊ አስታወቁ።
በጅማ ከተማ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉም ከ63 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ምግቦችና ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው።
ከድጋፎቹ ዉስጥ የዜጎችን ህይወት በቀጣይነት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ዘመናዊ የንብ ቀፎ እና የዶሮ ጫጩቶች ይገኙበታል።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ነመራ ቡሊ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግስት ካስቀመጣቸዉ አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ህይወት ማሻሻል ነዉ።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለውጥና ልማትን በማቀናጀት ስር የያዘ ስራ መስራትና የዜጎችን ህይወት መቀየር ነው ሲሉም አክለዋል።
አገልግሎቱ የመደጋገፍ ባህልን እያጎለበተና የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ እያሻሻለ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከህዝቦች ነባር ባህል ውስጥ አንዱ መረዳዳት ነዉ ያሉት አቶ ነመራ ባለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት በክልሉ ከ50 በላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መገንባታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለተማሪዎች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ድጋፍ ተደርጎ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከድህነት ለመውጣት በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው ያሉት አቶ ነመራ ከዓመታት በፊት ሲታገዙ የነበሩ ዜጎች ራሳቸውን ወደመቻል ተሸጋግረዋል ብለዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ ጠሀ ቀመር በበኩላቸው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን የመረዳዳት ባህል እና አንድነትን ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዛሬ ለተደረገው የበጎ ፈቃድ ተግባር አስተዋጽኦ ያደረጉ የጅማ ከተማ ባለሀብቶች እና ነዋሪዎችን እንዲሁም ተቋማትን አመስግነዋል ።