ቀጥታ፡

የ2018 የክረምት ወቅት የዘጠና ቀናት ዕቅድ በሁሉም መስኮች ውጤታማ ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦የ2018 የክረምት ወቅት የዘጠና ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም በሁሉም መስክ ውጤታማ ሆኖ እየተተገበረ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች የከተማ አስተዳደሩን የ2018 ክረምት የዘጠና ቀናት እና የበጎ ፍቃድ ስራዎች የዕቅድ አፈጻጸም ሂደትን ገምግመዋል፡፡


 

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በከተማዋ ብሎም በሀገሪቱ ባህል እየሆነ የመጣ መሆኑን የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለይም የክረምቱ ወቅት በዚህ መስክ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት እንደመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሌላው በክረምቱ ልዩ ትኩረት የተሰጠው የአረንጓዴ ልማት እና የከተማ ጽዳት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይም ጎርፍን የመከላከል እና የጎርፍ ማፋሰሻ መስመሮችን የማጽዳቱ ተግባር ስኬታማ ቢሆንም በከተማዋ ከሚካሄዱ መጠነ ሰፊ የግንባታ ስራዎች ጋር ተያይዞ የግንባታ ተረፍ ምርቶች አወጋገድ በተገነቡ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ ሰፊ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ከንቲባ አዳነች የተናገሩት፡፡


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከክረምት እቅዶች በመልካም የአፈጻጸም ሂደት ላይ ያለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ ጥራትን ለማስጠበቅ እና ለአንድ ጀምበር ተከላ ዝግጅት ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ሰብዓዊ ድጋፍ ከማጠናከር አንጻርም እስካሁን መልካም ጅምሮች እንዳሉ እና በቀጣይ በቂ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት ትኩረት እንደሚሰጥ  ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል፡፡

የተጀመሩ የቤት ግንባታዎችን ማፋጠን፣የፍሳሽ መውረጃዎችን ማጽዳት እና ተጨማሪ መገንባት፣ ከፍተኛ ሀብት ፈሶባቸው የለሙ ቦታዎችን መንከባከብ፣ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ማጠናከር እና ሌሎችም በክረምቱ የተያዙ እቅዶች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም