የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሽመልስ ኃይሉ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ከታሪካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዳራዎች አንፃር የተቃኘ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ከቀጣናዊ መረጋጋትና ደህንነት፣ ከሉዓላዊነትና ከኢኮኖሚ ልማት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሽመልስ ኃይሉ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትየቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም መሠረት ያደረጉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ የምሁራን መድረኮችን በማዘጋጀት ውጤታማ ሥራዎች መከናወኑን ተናግረዋል።
በተለይም የቀይ ባሕር ተጋሪ ሀገራት ምሁራንና አጋር አካላት በተገኙበት ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ መካሄዱን ጠቅሰዋል።
እነዚህ መድረኮች የኢትዮጵያን መሠረታዊ ጥያቄዎች፣ ምክንያቶችና ሀገሪቱ ፍላጎቷን ለማሳካት የምትችልበትን መንገድ ማመቻቸቱን አመልክተዋል።
በዘንድሮው ዓመት ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የመጡ ወጣት ዲፕሎማቶችን በመጋበዝ የልምድ ልውውጥና የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱን ጨምረው አስታውቀዋል።
ይህም በቀጣናው ሀገራት መካከል ያለውን ወንድማማችነትንና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከአፍሪካ ቀንድ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎች ሀገራት የመጡ ዓለም አቀፍ ምሁራንን በማሳተፍ በቀጣናው ሰላም፣ ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ላይ ጥናታዊ ውይይቶችን በማካሄድ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት ማቅረቡን አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና ቀጣናዊ ትስስር ላይ ያተኮሩ ከ10 በላይ ጥናቶችን በውስጥ እና በውጭ ምሁራን አስገምግሞ ይፋ እንዳደረገም ነው የተናገሩት።
በተካሄደው የኢኮኖሚ ሪፎርም መሠረት እስከዛሬ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የኢኮኖሚ ዕድሎችን በባለሙያዎች የማጥናት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ጥናቶቹ እነዚህን አቅሞች ወደ ኢንቨስትመንት ለመቀየር የትኞቹ ሀገራትና ተቋማት መሳተፍ እንዳለባቸው በመለየት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ መሠረት ያደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶችን በማካሄድ ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ዘላቂ እና ውጤታማ እንዲሆን በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን የኢኮኖሚና የልማት አቅም በመለየት የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል የሚያመላክቱ ጥናቶች መካሄዳቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ መሠረት በማድረግ ምርምር ማካሄድ፣ ለዲፕሎማቶች አስፈላጊውን ስልጠና መስጠትና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በጥናትና ምርምር መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ሽመልስ ኃይሉ አረጋግጠዋል፡፡